የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገር መከታነቱም ባለፈ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገር መከታነቱም ባለፈ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017 (ኢዜአ):- የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገር መከታነቱም ባለፈ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ መሆኑን የኢትዮጵያ የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ገለጹ።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ ለኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በተፈጥሮና አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የ5 ሚሊየን ብር የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል።
ድጋፉንም የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በሀገር መከላከያ ሠራዊት ከምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ጸጋዬ ተረክበዋል።
ኮሚሽነሩ በዚሁ ጊዜ ባደረጉት ንግግር፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰላምና ደኅንነትን ከማስጠበቅ ባለፈ በአስቸጋሪ ሁኔታም የዜጎች ፈጥኖ ደራሽ መሆኑን ገልፀዋል።
በዛሬው እለት የምስራቅ ዕዝ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከሀገር መከታነቱም ባለፈ የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ያለ የሕዝብ ልጅ መሆኑን ገልፀዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ ችግሮችን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት በሚደረገው ጥረት አጋርነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀው፤ ለአደጋዎች ቀድሞ የመድረስና አፋጣኝ ድጋፍ የመስጠት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል ፍቃዱ ጸጋዬ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ ግዳጅ ላይ የሚገኙ የዕዙ አባላት መዋጮ የተፈጥሮ አደጋ ላጋጠማቸው ወገኖች የሚውል የ5 ሚሊየን ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።
በቀጣይም የሠራዊቱ እገዛና ድጋፍ እንደማይለይ አረጋግጠው መከላከያ ሠራዊት የሀገር መከታነቱንና የሕዝብ አለኝታነቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልፀዋል።