የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል -አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል -አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ

አዲስ አበባ፤መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያና ሕንድ ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ ተናገሩ።
የሕንድ የነፃነት አባት በሚል የሚታወቁት ማህተማ ጋንዲ ወይም በሙሉ ስማቸው ሞሃንዳስ ካራምቻንድ ጋንዲ 155ኛ የልደት በዓል ዛሬ በጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ተከብሯል።
በመታሰቢያ በዓሉ ላይ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር የመንግስት ተጠሪዎች፣የሕንድ ማህበረሰብ አባላትና የሆስፒታሉ የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት አምባሳደር አኒል ኩመር ራሂ ሆስፒታሉ የሁለቱ አገራት ሁለንተናዊ ትብብር ማሳያ መሆኑን ገልጸው፥ለሆስፒታሉ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ማህተመ ጋንዲ ለሕንድ ነጻነት ከፍተኛ ሥራ የሰሩና አገሪቱን የመሩ ጀግኛ ነበሩ፣ ዛሬም ሥራቸው ሲታወስ ይኖራል ብለዋል።
በሕንድ የነፃነት ትግል ውስጥ የጋንዲ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አበርክቶ እንዲሁም ዘመን ተሻጋሪ እሳቤዎች ይንፀባረቃሉ በማለት ጠቁመዋል።
የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ ጤናና ማኑፋክቸሪንግን ጨምሮ በተለያዩ የኢንቨስትመንትና የንግድ ሥራዎች ጉልህ ተሳትፎ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
የሕንድ መንግስት የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል የሚሰጠውን አገልግሎት ለማጠናከር ይሰራል ብለዋል።
የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ታሪኩ ዴሬሳ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በዓመት 10 ሺህ ለሚሆኑ እናቶች የማዋለድ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም በዓመት ከአራት ሺህ በላይ ለሚሆኑ ጨቅላ ህጸናት አስተኝቶ የማከም አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግስት ደረጃ በእናቶችና ህጻናት ህክምና ግንባር ቀደም አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ጠቁመው፥ የህንድ መንግስትና ማህበረሰብ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።