ልብ ሊባል የሚገባው የልብ ህመም - ኢዜአ አማርኛ
ልብ ሊባል የሚገባው የልብ ህመም

"ልብ ሊባል የሚገባው የልብ ህመም "አሳሳቢነትና መፍትሔዎቹ በልብ ሕክምና ባለሙያዎች አንደበት።
በዓለም ላይ በተለይም አፍሪካን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት የልብ፣ የደምሥርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የጤና እክል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል።
በኢትዮጵያም በልብ፣ በደምሥርና ተላላፊ ባልሆኑ የበሽታ አይነቶች በርካታ ዜጎች በየቀኑ ለህልፈት እየተዳረጉ መሆኑን ባለሙያዎቹ ያነሳሉ።
ጤናማ ያልሆነ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ሱስ አምጪ ንጥረ ነገሮች፣ ስኳርና ጨው አብዝቶ መጠቀም ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች የሚያጋልጡ መሰረታዊ ምክንያቶች ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የሕክምና ሙያተኞች የልብና የደምሥር በሽታዎችን አስቀድሞ መከላከል እንደሚቻል ያስረዳሉ፡፡
ነገር ግን በሽታዎቹ ስር ከሰደዱ በኋላ በህመምተኞቹ ላይ የሚያስከትሉት ወጪና ስቃይ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የልብ ሐኪም ዶክተር ደጁማ ያደታ፤ የልብ ህመም በዓለም ላይ ቁጥር አንድ ገዳይ በሽታ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም በለጋ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ዜጎችን ከሚያጠቃ የጉሮሮ ቁስለት ህመም ጋር ተያይዞ የሚከሰት የልብ ህመም አሳሳቢነት ከፍተኛ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
በኤሊያና ኸልዝ ኬር የያኔት ሆስፒታሎች ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ግርማ አባቢ፤ የልብና የደምሥር በሽታ ከየትኛውም የህመም አይነት በላይ ለዜጎች ህልፈት መነሻ እየሆነ የመጣ አሳሳቢ የጤና እክል ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ የልብና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከልና የህክምና አገልግሎቱን ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የችግሩ ፍጥነትና ምላሽ የሚሰጥበት አካሄድ የተመጣጠነ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግስትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ዜጎችን ለከፍተኛ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና እየዳረገ የሚገኘውን የልብ፣ የደምሥርና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል በሰፊው መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የውስጥ ደዌና የአዋቂዎች የልብ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ከፈለኝ ደጀኔ በበኩላቸው የልብ ህክምና እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ ሀገራት ዜጎች በጣም ውድ በመሆኑ ቅድመ መከላከል ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
በታዝማ የውስጥ ደዌና ቀዶ ሕክምና ልዩ ማዕከል ጠቅላላ ሐኪም ዶክተር ኤልሻዳይ ሰለሞን፤ የልብ ህመም በተፈጥሮም ሆነ በሰዎች የእለት ከእለት የኑሮ ዘይቤ የሚከሰት በሽታ ነው ብለዋል።
በህፃናት ላይ የሚከሰት የጉሮሮ (ቶንሲል) ህመም ኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ ሀገራት ዜጎች የልብ ሕመም ተጋላጭነት ከፍተኛ እንዲሆን ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሰዎች ጭንቀትንና የኮሊስትሮል መጠን በመቀነስ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና የአመጋገብ ስርዓትን በማስተካከል ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከል እንደሚችሉ አስገንዝበዋል።
የልብና የደምሥር የህክምና ግብዓቶች ውድ በመሆናቸው የሚያስከትሉት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና ከፍተኛ መሆኑን የአይሲኤምሲ አጠቃላይ ሆስፒታል ማርኬቲንግ ዳይሬክተር ጌታቸው ኃይለስላሴ ተናግረዋል።
የልብ ህመም ድንገተኝነት ከፍተኛ በመሆኑ ዜጎች የተስተካከል የአመጋገብ ሥርዓት መከተልና የጤና ምርመራ ባህልን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል።
የልብ ሕክምና ጥቂት ሙያተኞች ያሉት ውስብስብ አገልግሎት ቢሆንም ከፍለው ከሚታከሙ ዜጎች ባሻገር አቅም ለሌላቸው ሰዎች በነፃ ህክምና አገልግሎት በመስጠት ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
መገናኛ ብዙሃንም የልብና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በማስመልከት ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው አንስተዋል።
በኢትዮጵያ የልብ ማኅበር አስተባባሪነት "ልብን ለተግባር እናውል" በሚል መሪ ሃሳብ በኢትዮጵያ ለ9ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ25 ጊዜ ዓለም አቀፉ የልብ ቀን በአዲስ አበባ መከበሩ ይታወሳል።