በመዲናዋ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ የሰላም ሰራዊት አባላት በብቃትና በንቃት እየተሳተፉ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ የሰላም ሰራዊት አባላት በብቃትና በንቃት እየተሳተፉ ነው
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):-በመዲናዋ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ የሰላም ሰራዊት አባላት በብቃትና በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ ተናገሩ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ያሰለጠናቸውን የሠላም ሰራዊት አባላት በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምርቃት ስነ ስርአቱ ላይ ንግግር ያደረጉት፤ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ፤ የሰላም ሰራዊት አባላት በመዲናዋ የሰላምና ጸጥታ ስራዎች ላይ በብቃትና በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ለከተማዋ አስተማማኝ ሰላም መኖር የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠቅሰው የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም ተጨማሪ አቅም መሆናቸውን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሸነር ጌቱ አርጋው፤ ለከተማዋ ሰላምና ጸጥታ መረጋገጥ የፖሊስ ኃይል ጠንካራ ስራ እንዳለ ሆኖ የሰላም ሰራዊትም ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
የሰላም ሰራዊቱና የፀጥታ አካላት ጠንካራ ቅንጅት እንዲሁም የነዋሪዎች ተሳትፎ የከተዋን ሰላም ዘላቂና አስተማማኝ ማድረግ አስችሏል ብለዋል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰላም ስራዊት አባላት፤ የነዋሪዎችን ሰላምና ደህንነት ይበልጥ አስተማማኝ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
ከመዲናዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተውጣጡት የሰላም ሰራዊት አመራሮችና አባላት በቆይታቸው የንድፈ ሃሳብና የመስክ ሥልጠና መውሰዳቸው ታውቋል።