በ2017 የትምህርት ዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል - የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ - ኢዜአ አማርኛ
በ2017 የትምህርት ዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል - የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ
አሶሳ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ በ2017 የትምህርት ዘመን በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ዝግጅት ማድረጉን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።
የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፕሬዝደንቱ ተወካይ መልካሙ ዴሬሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ የመማር ማስተማር ስራ ለማከናወን ዝግጅት አድርጓል።
ዲጂታል ቤተ መጻህፍት እና ዲጂታል የመማሪያ ክፍሎች ለመማር ማስተማር ስራው መዘጋጀታቸውንም አስታውቀዋል።
በዘንድሮው ዓመት ብቻ ስክሪን እና አስፈላጊ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች የተገጠመላቸው 10 ዲጂታል የመማሪያ ክፍሎች ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች ዲጂታላይዝድ የመማር ማስተማር ሥራውን በመተግበር ላይ መሆኑን በማከል።
ዩኒቨርሲቲው በአካባቢው ያለውን ሀብት እና የሰው ኃይል በማቀናጀት ሁሉን አቀፍ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራም መልካሙ (ዶ/ር) ገልፀዋል።
የማዕድን እና የግብርና ስራዎችን ማዘመን የዩኒቨርሲቲው ዋነኛ ትኩረት እንደሆነ በመጠቆም።
ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማር ስራው በተጨማሪ በግብርና እና እርሻ ተስማሚነት ላይ የምርምር ስራዎችን እንደሚያከናውንም ገልፀዋል።
በተለይም በቆላማ አካባቢ ባሉ የግብርና ልማቶችና በመስኖ ላይ ትኩረት አድርጎ የምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑንም አክለዋል።
ዩኒቨርስቲው በ2016 የ12ኛ ክፍል ፈተና እና ሌሎች ሀገር አቀፍ ስልጠናዎችን በብቃት ማስተናገዱን አስታውሰዋል።
በ2004ዓ.ም የመማር ማስተማር ስራውን የጀመረው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቹን እስከ መስከረም ወር መጨረሻ በመቀበል ላይ ነው።