ቀጥታ፡

የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ውጤታማ ሆነው ለመቀጠል ተፈጥሮን ከሳይንሳዊ እውቀቶች ጋር ያጣመረ መንገድ መከተል አለባቸው - የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):- የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች ውጤታማ ሆነው ለመቀጠል ተፈጥሮን  ከሳይንሳዊ እውቀቶች ጋር ያጣመረ መንገድን መከተል አለባቸው ሲሉ  የስፖርት ሳይንስ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡

"ኢትዮጵያ የአሸናፊዎች ምድር" በሚል መሪ ሀሳብ  ከሰኔ 13 ቀን 2016 ዓ.ም አንስቶ በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሲስ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቶች የፎቶ አውደ ርዕይ ትናንት ማምሻውን ተጠናቋል።


 

የኢትዮጵያ አትሌቶችን በማስታወስና በማክበር ሌሎችን ማነሳሳትና ሕልማቸውን እንዲያሳኩ ማበረታታት የአውደ ርዕዩ አላማ ነው።

በመዝጊያ መርሃ ግብሩ ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በከፍታ ቦታ በሚሰሩት ልምምድ ያዳበሯቸው ክህሎቶችና ያጋጠሟቸውን ፈተናዎችን አስመልክቶ የመነሻ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ እና ኮምፒዩቴሽናል ሳይንስ ኮሌጅ የስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዘሩ በቀለ (ዶ/ር) ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ልምምድ የሚሰሩባቸው የከፍታ ቦታዎች እና ተፈጥሯዊ አቅማቸው በውድድር ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

አትሌቶች ከፍታ ካለባቸው አካባቢዎች መምጣታቸው በአነስተኛ ኦክስጂን መተንፈስን እንዲለማመዱና ይህም በሩጫ ወቅት ከባህር ወለል ወይም ከዚያ ዝቅ ካለ ከፍታ ከሚሮጡ ሯጮች የበለጠ ጥንካሬ እንዲያዳብሩ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በከፍተኛ ቦታ ላይ መሮጥ የእግር ጡንቻ ጥንካሬን እንደሚያጎለብትም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያላቸው የተፈጥሮ ተነጻጻሪ ጥቅም ብቻውን በዘላቂነት ውጤታማ እንደማያደርጋቸው ገልጸው ስልጠናና ልምምዳቸው ይበልጥ ከሳይንሱ ጋር የተቆራኘ መሆን እንዳለበት ገልጸዋል።

በከፍታ ቦታ ብቻ ሳይሆን በዝቅተኛ ስፍራዎች ልምምድ በማድረግ እና ስልጠና በመውሰድ በሁለቱም መልክዐ ምድሮች ላይ ውጤታማ የሚሆኑበትን አካሄድ መከተል እንደሚገባቸው ነው ዶክተር ዘሩ ያስረዱት።

አትሌቶች ከአካል ብቃት ስልጠና፣ አመጋገብ ባሻገር በስነ ልቦናና አዕምሮ ዝግጁነት ላይም በትኩረት መስራት እንዳለባቸው መክረዋል።

የኬንያው ኪኤስኤ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት እና የአካል ብቃት ሳይንስ ፕሮፌሰር ቪንሰንት ኦንዌራ የተፈጥሮ ብቃት እና የከፍታ ቦታ ለኬንያና ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ለምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች የረጅም ርቀት ውጤታማነት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ተናግረዋል።


 

የማህበረሰብ አኗኗር ዘይቤና ስነ ልቦና ለአትሌቶች ውጤታማነት የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ይሁንና የዓለም አትሌቲክስ አሁን ከደረሰበት ደረጃ አኳያ ተፈጥሯዊ አቅም ብቻውን አሸናፊ እንደማያደርግ በመገንዘብ ተፈጥሮን ከሳይንሳዊ ስልጠናና ምርምር ጋር በማቆራኘት ቀጣይነት ላለው ውጤታማነት መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ የከፍታ ቦታዎችን ተፈጥሯዊ ሃብት እየበከለ በመሆኑ በአትሌቶች ልምምድ ላይ የራሱ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን አንስተዋል።

ይህንን ፈተና ለመሻገር በአሁኑ ሰዓት ለከፍተኛ አካባቢዎች አማራጭ የሆነውን በዝቅተኛ የኦክስጅን መጠን የከፍተኛ ቦታ ምስለ ድንኳን (altitude tent simulation) እንደ አማራጭ መጠቀም እንደሚቻል አንስተዋል።

የፈረንሳዩ ቬርሳይልስ ሴይንት ኩዌንቲን ቬሊነስ ዩኒቨርሲቲ ማህበራዊ ሳይንቲስት እና የስፖርት ሳይንስ ተመራማሪ ቤንዋ ጋውዲን ተፈጥሮ ፣ የከፍታ ቦታ እና የዘረመል አወቃቀር ብቻውን አትሌቶችን ውጤታማ እንደማያደርግ ገልጸዋል።


 

ተፈጥሯዊ አቅሞችን ከሳይንሳዊ እውቀት፣ ዘመናዊ ስልጠና፣ ጠንካራ ስራ እና ስነ ልቦናዊ አቅምን ከማጎልበት ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የምስራቅ አፍሪካ አትሌቶች በአትሌቲክስ ውድድሮች ከተቀረው የዓለም ክፍል ከሚገኙ አትሌቶች ጋር በብቃት ለመወዳደር ሁሉን አቀፍ ክህሎቶችን ማዳበር እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

አውደ ርዕዩ በስድስት የኢትዮጵያ እና የፈረንሳይ ፎቶግራፍ ባለሙያዎች የቀረበ ነው።

የፎቶግራፍ አውደ ርዕዩን በማስመልከት እ.አ.አ በ2012 የተለቀቀው 'Town of Runners' የተሰኘው የስፖርት ዶክመንተሪ ለፕሮግራሙ ታዳሚያን ቀርቧል።

በእንግሊዛዊው የዶክመንተሪ ፊልም ባለሙያ ጄሪ ሮትዌል የተሰራው የ1 ሰዓት ከ20 ርዝማኔ ያለው ዶክመንተሪ  የኢትዮጵያ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ ከተማ የሚገኙ ሶስት ሕጻናት ከከተማዋ ተነስተው በኦሊምፒክ ጨዋታዎች እና የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመድረስ ያስመዘገቡትን ውጤትና ጉዞ የሚያስቃኝ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም