ቀጥታ፡

በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲመጣ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተመለከተ

ሠመራ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ)፦ የሐሳብ ልዩነትን አጥብበን በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት እንዲመጣ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ጉልህ አስተዋጽኦ እንሚያደርግ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሸን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ትናንት ማካሄድ መጀመሩ ይታወሳል።

የኮሚሸኑ ኮሚሽነር ብሌን ገብረ መድህን ለኢዜአ እንደተናገሩት እየተካሄደ ያለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚፈጠርባቸው ሀሳቦች የሚነሱበት ነው።

በዚህ የሚሳተፉት የማህበረሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት አንድ ላይ ቁጭ ብለው የተለያዩ ጉዳዮችን በማንሸራሸር አንኳር ጉዳዮችን ነቅሰው የሚያወጡበት እንደሆነም አንስተዋል።

የመደማመጥ ባህላችንን ተጠቅመን በምክክሩ ሒደት ሐሳቦችን በማንሸራሸር የጋራ ጥያቄዎቻችን ላይ መግባባት ላይ ከተደረሰ ሂደቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ጉልህ ሚና አለው ብለዋል።

ኮሚሸነር ብሌን እንዳሉት በአፋር ክልል በአጀንዳ ማሰባሰብ ላይ የጀመርናቸው ምክክሮች ለአጠቃላይ ሀገራዊ ምክክር ሂደቱ መሳካት አስፈላጊ ግብዓት የሚገኝበት ይሆናል።

በዚህ የምክክር መድረክ ወጣቶች፣ መምህራን፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት በንቃት በመሳተፍ የጋራ ጉዳዮችን ነቅሰው በማውጣት ሂደቱን የሚያግዙበት መሆኑን አስረድተዋል።

ይህ የምክክር ምዕራፍ ሂደት የጋራ መግባባት የሚፈጥርባቸው አጀንዳዎች የሚነሱበት በመሆኑ ሁሉም በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በአፋር ክልል የተጀመረው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት ከ49 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ነው የሚካሄደው።

የምክክር ሂደቱ ለስድስት ቀናት በሚኖረው ቆይታ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው ውይይት እንደሚካሄድ እና ሀሣቦች እንደሚያንሸራሽሩ የወጣው መርሃ ግብር አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም