የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኝነት የማረጋገጥ አገልግሎትን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኝነት የማረጋገጥ አገልግሎትን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ መስከረም 22/2017(ኢዜአ):- የመለኪያ መሳሪያዎች ትክክለኝነት በማረጋገጥ የህብረተሰቡን ጤናና የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ስነ-ልክ ኢንስቲትዩት አለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን የልኬት አሃዶች መሰረት በማድረግ የልኬት ትክክለኝነትን የሚያረጋግጥ ተቋም ነው፡፡
እንደዚሁም የስልጠና፣ የቴክኒክ ድጋፍ፣ የሳይንስ መሳሪያዎች ጥገና፣ የክብደት፣ የሙቀት፣ የግፊት፣ የግዝፈት፣ የሚዛን፣ የሃይል፣ የጨረራና የመጠን አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
በዋነኝነት በጤና፣ በግንባታ፣ በኢንዱስትሪ፣ በኤሌክትሪክ፣ በምርምርና በሌሎች ተቋማት የሚገኙ የልኬት መሳሪያዎችን ትክክለኝነት የማረጋገጥና የሳይንስ መሳሪያዎች የጥገና አገልግሎት ይሰጣል፡፡
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍቅረአብ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአመት ከ2 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ደንበኞች በደሴ፣ በባህርዳር፣ በሃዋሳ፣ በድሬዳዋና በጅማ ቅርንጫፎች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በየወሩ በአማካይ 3ሺህ ለሚደርሱ የተለያዩ መሳሪያዎች የልኬት ትክክለኝነት እየተረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በንግድ፣ ኢንዱስትሪና በምርምር ዘርፍ የሚመረቱ ምርቶች ጥራታቸው የተጠበቀና ልኬታቸው የተስተካከለ ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
ጥራትና ደህንነቱ ባልተጠበቀ መመርመርያ መሳሪያና መለኪያ መጠቀም በህብረተሰብ ጤናም ሆነ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ሊያደርስ የሚችለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ወደ ውጭ የሚላኩና ወደ ሀገር የሚገቡ ምርቶች መጠንና ይዘትን በሚመለከት ልኬታቸው የተስተካከለ እንዲሆን ኢንስቲትዩቱ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በ15 ሚሊየን ዶላር የጨርቃ ጨርቅ፣የቆዳና የምግብ ኢንዱስትሪዎችን ማምረቻ መሳሪያዎች ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልኬት መሳሪያዎችን በመግዛት ወደ ስራ ለማስገባት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትየጵያ ከ350 ሺህ በላይ የልኬት መሳሪያዎች እንደሚገኙ ገልጸው፤ ይህም መረጃ የሚያመለክተው ከተደራሽነት አንጻር ብዙ መስራት የሚጠበቅ መሆኑን ነው ብለዋል፡፡