የአገልግሎቱ ሰራተኞችና የአመራር አባላት በዎንሾ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ - ኢዜአ አማርኛ
የአገልግሎቱ ሰራተኞችና የአመራር አባላት በዎንሾ ወረዳ በደረሰ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ አደረጉ
ሐዋሳ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰራተኞችና አመራር አባላት ከ436 ሺህ ብር በላይ በመሰብሰብ በዎንሾ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ዜጎችና በይርጋለም ከተማ ለሚገኙ ህጻናት የተለያዩ ድጋፎችን አደረጉ።
የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ባንተአየሁ ቀጸላ በድጋፉ ርክክብ ወቅት እንዳሉት፤ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለማገዝ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ ነው።
ለዚህም እቅድ ተነድፎ ተጎጂዎችን በዘላቂነት ለማገዝ ከተቋማት ጋር በመቀናጀት የተጀመረው ድጋፍ መቀጠሉን ጠቅሰው፤ የሲዳማ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ድጋፍም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበበ እድሉ ለተፈናቃዮቹ ድጋፉን ባስከረከቡበት ወቅት እንደገለጹት አገልግሎቱ ከኤሌክትሪክ ስርጭቱ ባሻገር ማህበራዊ ሃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ ነው።
ዛሬም ከአገልግሎቱ ሰራተኞችና ሃላፊዎች የተሰበሰበ ከ436 ሺህ ብር በላይ በሲዳማ ክልል ዎንሾ ወረዳ በደረሰ መሬት መንሸራተት አደጋ ለተፈናቀሉ ወገኖች እና በይርጋለም ከተማ ለሚገኙ የአቅመ ደካማ ቤተሰብ ህጻናት ድጋፍ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በዚህም 112 ለሚደርሱ ተፈናቃይ ቤተሰቦች የምግብ ዘይትና ዱቄት፤ ከ250 ለሚበልጡ ህጻናት ደግሞ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በመሬት መንሸራተት አደጋው የእርሻ ማሳቸው እንደወደመባቸው የተናገሩት አቶ ታዬ ታደሰ በበኩላቸው የተለያዩ ተቋማት እያደረጉላቸው ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በሲዳማ ክልል ዎንሾ ወረዳ ሐምሌ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።