ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የቀድሞ መኖሪያ ቤት እድሳትን ጎበኙ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ለጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከል የተዘጋጀውን የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የቀድሞ መኖሪያ ቤት እድሳት ጎብኝተዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ ለጣይቱ የባህልና ትምህርት ማዕከልነት የተዘጋጀውን የቢትወደድ ኃ/ጊዮርጊስ ወ/ሚካኤል የቀድሞ መኖሪያ ቤት እድሳት ጎብኝተናል ብለዋል።

መኖሪያ ቤታቸው የተገነባው ከ119 ዓመታት በፊት እንደነበር ጠቅሰው፤ ቅርስ ሀብታችን ነው፤ ግን ሁለት ነገር ይፈልጋል፤ ማቆየትና ማዘመን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ማቆየት ማለት ለትውልድ እንዲተላለፍ አድርገን መጠገንና ማሣመር መሆኑን የገለጹት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማዘመን ደግሞ ይሄንና መጪውን ዘመን እንዲያገለግል አድርጎ ማስተካከል መሆኑን አብራርተዋል፡፡


 

ቅርስነቱ እንደተጠበቀ ለጉብኝት ማመቻቸት፤ መብራትና ውኃውን ማስተካከል፤ የኢንተርኔት መሥመሩን መዘርጋት፤ ለነገ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ነው፡፡ አሮጌውን አትንኩት በሚል እስኪፈርስ እያዩ ማጥፋት አይደለም ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

ይህ ሕንጻ ለዚህ ምሳሌ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንቱ ማቆየት ያለብን አለ፤ ለዛሬና ለነገ ስንል ደግሞ ማፍረስ ያለብን አለ ብለዋል፡፡

ብልጽግና ትናንትን ከነገ ጋር ማስማማት ነው፤ትናንት ለነገ ዕንቅፋት ከሆነ ይፈርሳል፤ ትናንት ለነገ ወረት ከሆነ ይጠበቃል፤ ይለማል ሲሉም አክለዋል፡፡

ይህ እድሳት ዳያስፖራዎች በሀገራቸው ሊኖራቸው የሚገባውን በጎ ተሳትፎ የሚያመለክት መሆኑን ጠቅሰው በማኅበራዊ ሚዲያ የሚገነባ ሀገር የለም ብለዋል፡፡

በሰልፍ የሚገነባ ሀገር የለም፤ ሀገር የሚገነባው ወገብ አሥሮ፤ አፈር ነክቶ ሥራ በመሥራት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ጉልበትን አፍስሶ ለመጭው ትውልድ የምትመች ሀገር በመሥራት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው ከያኒት ዓለምፀሐይ ወዳጆ ያደረገችውም ይሄንኑ ነው፤ ለዚህ ተምሳሌታዊ ሥራ እናመሰግናለን ብለዋል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም