የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያስተናገዳቸው 14 ሚሊዮን መንገደኞችና በርካታ ጭነቶች ያለ ምንም የደኅንነት ስጋቶችና ክፍተቶች እንዲጓጓዙ በማድረግ ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተገለፀ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያስተናገዳቸው 14 ሚሊዮን መንገደኞችና በርካታ ጭነቶች ያለ ምንም የደኅንነት ስጋቶችና ክፍተቶች እንዲጓጓዙ በማድረግ ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተገለፀ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያስተናገዳቸው 14 ሚልዮን መንገደኞችና በርካታ ጭነቶች ያለ ምንም የደኅንነት ስጋቶችና ክፍተቶች እንዲጓጓዙ በማድረግ ረገድ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ሚና ከፍተኛ እንደነበር ተገለፀ ።
ለዚህ ስኬት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የአገልግሎት መሥሪያ ቤቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እውቅና እንደተሰጣቸው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ እንዳመለከተው፤ ተቋሙ ከተሰጡት ቁልፍ ተልዕኮዎች ውስጥ በኢትዮጵያ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ደኅንነት የተረጋገጠ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡
በዚህም በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የጎላ ስም ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ያስተናገዳቸው 14 ሚልዮን የሀገር ውስጥና ዓለምአቀፍ መንገደኞችና ትላልቅ ጭነቶች ያለ ምንም የደኅንነት ስጋቶችና ክፍተቶች እንዲጓጓዙ ማድረግ ተችሏል፡፡
ተቋሙ የአቪዬሽን ደኅንነትን ለማረጋገጥ የሚሠማሩ ባለሙያዎችን በማሰልጠን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ በማዋልና በተጓዦችና በንብረቶች ላይ ተገቢውን የደኅንነት ፍተሸ በማድረግ በ2016 በጀት ዓመት ምንም አይነት የደኅንነት ስጋቶች እንዳይኖሩ ማድረጉን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ ጠቁሟል፡፡
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ እና የደኅንነት ልዩ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ የ2016 በጀት ዓመት የማጠቃለያና የሠራተኞች ማበረታቻ መርኃ-ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ የበረራ ደኅንነትን በማረጋገጥ ረገድ የተገኘው ስኬት መላው አመራሮችና አባላት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌሊትና ቀን በመሥራት የተገኘ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በዚህ ዓመት የተገኘው ስኬት የሚያዘናጋን ሳይሆን በቀጣይ ሊገጥሙን ከሚችሉ ውስብስብ የበረራ ደኅንነት ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችል የሞራል ስንቅ ሊሆነን ይገባል ብለዋል፡፡
በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የደኅንነት ዘርፍ ለተገኘው ስኬትና በደኅንነት ልዩ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ በኩል ለተገኘው እመርታ ርብርብ ላደረጉ የሥራ ክፍሎች፣ ሠራተኞችና ባለድርሻ አካላትም ምስጋና ያቀረቡት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን የተጀመረው ሁሉን አቀፍ ጥረትና ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሲሳይ ቶላ በበኩላቸው፤ አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመቀናጀት በአፍሪካ ቀዳሚ የአቪዬሽን ደኅንነት አገልግሎት እንዲገነባ ለማድረግ የጀመረውን ሁሉን አቀፍ ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል መግለፃቸውን ያመለከተው የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ መረጃ፤ ከ12 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ኦዲት ያደረገው ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ኢትዮጵያ ምንም አይነት የአቪዬሽን ደኅንነት ሥጋት የሌለባት ሀገር ናት ማለቱ የስኬቶቹ ማሳያ እንደሆነ መናገራቸውን አስታውቋል፡፡
የደኅንነት ልዩ ኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ባለሙያዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ መደረጉን የገለፁት አቶ ሲሳይ ቶላ በአዲስ አበባ የተካሄደው 37ኛው የመሪዎች ጉባኤ፣ ሃይማኖታዊና ህዝባዊ ባዕላትን ከበርካታ ሀገራት የመጡ የሀገር መሪዎችን፤ እንዲሁም ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት እና አመራሮችንና በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ በደኅንነቱ መስክ የተገኙ የዓመቱ ስኬቶች እንደሆኑም ጭምር መግለፃቸውን መረጃው አመልክቷል፡፡
የሲቪል አቪዬሽን ደኅንነት ዋና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ በበኩላቸው፤ በዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው ስጋት አንጻር ቀድሞ በመዘጋጀት የደኅንነት ስጋቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ መግታት ተችሏል ብለዋል፡፡
በኤርፖርት ተጓጉዘው በሀገርና በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ የነበሩ ሕገ-ወጥ የጦር መሣሪያዎች፣ የቴክኖሎጅ ውጤቶች፣ አደንዛዥ እጽ፣ ሕገ-ወጥ ገንዘብ ፣ የከበሩ ማዕድናት እንዲሁም ለሽብር ዓላማ ይውሉ የነበሩ ድሮኖችን ጭምር በቁጥጥር ሥር ማዋልና ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ለተመዘገበው ስኬት የላቀ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እውቅና እንደተሰጣቸው ያመለከተው የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፤ እውቅና ከተበረከተላቸው ከእነዚህ ባለድርሻ አካላት መካከልም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር አንዱ መሆናቸውን አገልግሎት መስሪያ ቤቱ ለመገናኛ ብዙኃን በላከው መረጃ አመልክቷል፡፡