ለአብሮነትና ለወንድማማችነት መጠናከር አቅም የሆኑ ባህላዊ ዕሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና እንዲሸጋገሩ አንሰራለን - የ"ማሽቃሬ ባሮ" በዓል ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
ለአብሮነትና ለወንድማማችነት መጠናከር አቅም የሆኑ ባህላዊ ዕሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና እንዲሸጋገሩ አንሰራለን - የ"ማሽቃሬ ባሮ" በዓል ተሳታፊዎች
ሚዛን አማን ፤መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፡- ለአብሮነትና ለወንድማማችነት መጠናከር አቅም የሆኑ ባህላዊ ዕሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩና ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የበኩላቸውን እንደሚወጡ በሸካቾ የዘመን መለወጫ "ማሽቃሬ ባሮ" በዓል ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የሸካቾ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሬ ባሮ" በተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች በሸካ ዞን ጊጫ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል የሀገር ሽማግሌው አቶ ብርሃኑ ማሪቶ እንዳሉት የ"ማሽቃሬ ባሮ" በዓልን ለማክበር አስቀድሞ ከተጣሉት ሰው ጋር ሰላምና ዕርቅ ማውረድ ያስፈልጋል።
ይህም በህዝቦች መካከል አብሮነትና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸው፤ ባህሉ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲሸጋገር የተጀመሩ ጥረቶች ስኬታማ እንዲሆን የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከበዓሉ እሴቶች መካከል አንዱ ከህብረተሰቡ ባህልና ወግ ውጭ የሆኑ ተግባራት በመገምገም እንዲታረም የሚደረግበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የ"ማሽቃሬ ባሮ" በዓልን ባህላዊ ዳራ በታሪክ ብቻ ይሰማ እንደነበርና በበዓሉ በተግባር የማየት ዕድል በማግኘቱ መደሰቱን የተናገረው ሌላው የበዓሉ ታዳሚ ወጣት ፍቅረዓለም ሻሪፎ ነው።
ዘንድሮ ጊጫ ከተማ ከተከበረው የ"ማሽቃሬ ባሮ" ክንውኖች ስለበዓሉ እሴቶች ብዙ መማሩን ገልጾ፣ "ባህላዊ እሴቶቹ ተጠብቀው ለትውልድ እንዲሸጋገሩ የበኩሌን እወጣለሁ" ብሏል።
አቶ አስታውሰኝ እንደሻው የተባሉ የበዓሉ ታዳሚ በበኩላቸው በ"ማሽቃሬ ባሮ" ሥነ ሥርዓት ውስጥ ያለው የምስጋናና የመከባበር ዕሴት ለሰላምና ለአብሮነት መጠናከር ሚናው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
"ማሽቃሬ ባሮ" ታላላቆችን ከማክበር ጀምሮ መመሪያና ህግን አክብሮ የሚተዳደር ትውልድ በመፍጠር ሰላምና መከባበርን የሚያጠናክር መሆኑን አክለዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ "ባህል የትናንት ታሪክና ማንነትን በማሳየት ለወደፊት የተሻለ ነገር ለመሥራት የሚያስችል አቅም አለው" ሲሉ ገልጸዋል።
በህብረተሰቡ መካከል አብሮነትና ወንድማማችነትን ለማጠናከር አቅም ያላቸው ቱባ ባህሎችና እሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ለትውልድ እንዲሸጋገሩና ለቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ ከማስተዋወቅ ጀምሮ የመሰነድ ሥራዎች ትኩረት እንደተሰጣቸውም አመልክተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ በበኩላቸው፤ በክልሉ ያሉትን ሀብቶች መጠበቅ፣ ማልማትና ለትውልድ ማሸጋገር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።
"ያሉን ብዝሃ ባህሎች መቻቻልና አብሮነትን በማጠናከር ልማትን ለማፋጠን ያላቸው አስተዋጾ የጎላ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።
የለውጡ መንግስት ለባህላዊ እሴቶች የሰጠውን ትኩረት ተከትሎ የተደበቁ የብሔር ብሔረሰቦች ባህላዊ በዓላት በአደባባይ እየተከበሩ መሆኑን ገልጸው፣ ይህም ባህላዊ እሴቶችን ለማስተዋወቅና ለትውልድ ለማሸጋጋር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
"ማሽቃሬ ባሮ" የዘመን መለወጫ በዓል ዩቦ፣ ቲሞና ሼሮ በተሰኙ ባህላዊ ክዋኔዎች የሚደምቅ ሲሆን፣ በዓሉ በአንድራቻ ወረዳ ጊጫ ከተማ የአካባቢው ተወላጆች፣ የሥራ ሃላፊዎችና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት ተከብሯል።