በቦረና የነበረው ድርቅ በአርብቶ አደርነት ብቻ ከመኖር እሳቤ በመውጣት ወደ ግብርና ልማትም እንድንገባ አድርጎናል - የአካባቢው ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በቦረና የነበረው ድርቅ በአርብቶ አደርነት ብቻ ከመኖር እሳቤ በመውጣት ወደ ግብርና ልማትም እንድንገባ አድርጎናል - የአካባቢው ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ በቦረና የነበረው ድርቅ በአርብቶ አደርነት ብቻ ከመኖር እሳቤ በመውጣት ወደ ግብርና ልማትም እንድንገባ አድርጎናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።
በቦረና በርካታ አርብቶ አደሮች በእንስሳት እርባታ የሚተዳደሩ ሲሆን አንድ አርብቶ አደር እስከ 400 ከብቶችን ሊያረባ እንደሚችል ይነገራል።
የቦረና ምድር በሦስት ተከታታይ ዓመታት በደረሰበት የድርቅ አደጋ ምክንያት በአካባቢው በተለይም በእንስሳት ላይ የደረሰው ጉዳት የብዙዎች የቅርብ ጊዜ ትዝታ ሆኖ ይታወሳል።
በወቅቱ የድርቁን አደጋ ለመቋቋምም መንግሥት ከተለያዩ ማዕዘናት ሕዝቡን በማስተባበር ርብርብ በማድረግ ከብዙ ጥፋቶች መታደግ የቻለበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ቦረና ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ሰሞኑን ባደረገው ምልከታ አካባቢው ከነበረው ችግር ወጥቶ ማሳው በሰብል ተሸፍኖ፣ ጋራ ሸንተረሩ አረንጓዴ ሆኖ ነዋሪዎች በጥሩ የኑሮ ሂደት ላይ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የአካባቢው ነዋሪዎችም የትናንት ችግር አልፎ ዛሬ ሌላ የደስታ ቀን ሆኖ በፍቅርና በደስታ እየኖርን ነው ብለዋል።
በዞኑ የማዶ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ቡልልቱ ቦሩ እና የደንቢሀራ ቀበሌ ነዋሪዋ ደሀቦ ገልማ፤ በድርቁ ሳቢያ በእያንዳንዳችን ቤት በተለይም እንስሳትን በመግደል ብዙ አሳጥቶናል ሲሉ ተናግረዋል።
ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የቆየው ድርቅ የቦረና እና አካባቢውን ኃብት ያሳጣ ሲሆን፤ በደንቢሀራ ቀበሌ ብቻ በርካታ የቀንድ ከብቶችን እንዳሳጣ ይናገራሉ።
በዞኑ የደንቢሀራ፣ የኮበላ እና የማዶ ቀበሌ ነዋሪዎቹ ሁቃ ዲዳ፤ ሼቅ አብደላ እና ቡልልቱ ቦሩ፤ በችግሩ ሳቢያ ብዙ ጉዳት ቢደርስብንም ትምህርት የወሰድንበት አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረውን የአርብቶ አደርነት ህይወት በማሻሻል ወደ እርሻ ሥራ በመግባት አሁን ላይ አምራቾች ሆነናል ሲሉ ተናግረዋል።
በግብርናው ዘርፍ በማኅበር በመደራጀት በተለያዩ የግብርና ምርቶች፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በንብ ማነብ ጭምር የህይወት ለውጥ በማምጣት ከተረጅነት ወደ ገበያ አቅራቢነት መሸጋገራቸውን ገልፀዋል።
የድሬ ወረዳ ነዋሪው ቄስ ግርማ ገላኔ እና የያቤሎ ከተማ ነዋሪው ጌቱ አበበ፤ ከድርቁ በርካታ ችግሮችና ፈተናዎች በመውጣት አሁን ላይ ወደ ልማትና ምርታማነት ተሸጋግረናል ብለዋል።
ከዓመታት በፊት ከነበረው ድርቅና ችግር ትምህርት በመውሰድም በግብርና እና የእንስሳት መኖ ልማት የተሳካ ውጤት አምጥተናል ሲሉ ተናግረዋል።