የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር ምክክር ለማድረግ ተዘጋጅቷል - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተወሰኑ ሀገራት በመጓዝ በውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር የፊት ለፊት ምክክር ለማድረግ መዘጋጀቱን ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር በውጭ ከሚኖሩና ይኖሩ ከነበሩ ዜጎች ያሰባሰበውን አጀንዳና በሀገራዊ ምክክሩ ላይ ያዘጋጀውን የሙዚቃ ክሊፕ(መዝሙር) ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስረክቧል።


 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ የልዩነት ጉዳዮች ላይ መቀራረብ እንዲፈጠር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን በዚሁ ሁነት ላይ ገልጸዋል።

የአሠራር ሥርዓት መመሪያ በመዘርጋት ከሀገር ውስጥ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ መሰራቱን አንስተዋል።

በዚህም በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በሌሎች ክፍላተ-ዓለማት ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር ከአሥር በላይ የበይነ-መረብ ምክክር ተካሂዷል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት መሥራት ይጠበቅብናል ያሉት ፕሮፌሰር መስፍን፤ በርካታ ሀገራት የውስጥ ችግራቸውን በምክክር እልባት በመስጠት የተሻለ ሰላምና ኢኮኖሚ መገንባት መቻላቸውን ጠቅሰው የኢትዮጵያም ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ እየሰራን ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ እስካሁን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ከተሞች አጀንዳ የማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ ማካሄዱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር የተረከበው የሙዚቃ ክሊፕ (መዝሙር) በሚያስተላልፈው መልዕክት የምክክር ሂደቱን እያስገነዘበ የሚገኝ ወሳኝ ሥራ በመሆኑ ዋና ኮሚሽነሩ ምስጋና አቅርበዋል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ አሉኝ የሚሏቸውን አጀንዳዎች በጋራም ሆነ በተናጠል ለኮሚሽኑ መላክ ይችላሉ ብለዋል።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች በተወሰኑ ሀገራት በመጓዝ በውጭ ከሚኖሩ ወገኖች ጋር የፊት ለፊት ምክክር ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።


 

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር የቦርድ አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ ኮሚሽኑ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ሁለንተናዊ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር ፕሬዝዳንት አርቲስት ዘለቀ ገሠሠ፤ ሰላም ለኪነ-ጥበብ ሥራ ወሳኝ በመሆኑ የምክክር ባህልን የማጎልበት ይዘትና ዓላማ የተላበሰ የሙዚቃ ሥራ ለምክክር ኮሚሽኑ ሰርተን አስረክበናል ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም