በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጀመሩ የህግ ማስከበር ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ባህር ዳር፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥና ተጠያቂነትን ለማስፈን የተጀመሩ ህግ የማስከበር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የመከላከያ ሠራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለፁ።

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው ጋር በመሆን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሎኔል ጌትነት አዳነ በመግለጫቸው እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ዋና ተልዕኮው ከውጭና ከውስጥ ጠላት ሊቃጣ የሚችል ጥቃትን በመከላከል ሉዓላዊነቷ የተከበረች አገር መገንባት ነው።

በአማራ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር የሚፈፀመውን ግፍና በደል ለመግታት የመከላከያ ሰራዊቱ የህግ ማስከበር ስራ ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል።

በዋና ዋና እና ትናንሽ ከተሞች ጭምር የህግ ማስከበር ስራ ከመስራት ባለፈ ከክልሉ ህዝብ ጋር ሰፊ ውይይት በማካሄድ ከግጭት ትርፍ እንደማይገኝ መተማመን ላይ መድረሱን ገልፀዋል።

አሁን በክልሉ የሚታየው ችግር ጽንፈኛው ቡድን ፀረ ህዝብ፣ ዓላማ የሌለውና የክልሉን ህዝብ የማይመጥን ተግባር ላይ የተሰማራ ከመሆኑም በላይ ለሰላም ደንታ እንደሌለው በተግባር አሳይቶናል ብለዋል።

የፌዴራልና የክልሉ መንግስታት በተደጋጋሚ ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ለውይይትና ንግግር ቢጥሩም ፅንፈኛ ቡድኑ ግጭትን በዋና አማራጭነት በመውሰድ በዝርፊያ፣ ግድያና ሌሎች እኩይ ተግባራት ላይ ተሰማርቷል።

ይሄን እኩይ ተግባር ለመጨረሻ ጊዜ ለመግታት መረቡን መበጣጠስ የሚያስችል የተጠና እርምጃ መውሰድ መጀመሩንም ተናግረዋል።

ጠላት የውስጥም ሆነ የውጭ ያው ጠላት ነው ያሉት ኮሎኔል ጌትነት፤ በቡድኑ ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ክልሉን ወደ ተሟላ ሰላም ለመመለስ የተጀመረው ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ለዚህም በመረጠው ቋንቋ ማነጋገር ተገቢ ሆኖ በመገኘቱ የመከላከያ ሰራዊት ኦፕሬሽን በእቅድና በዝግጅት ላይ ተመስርቶ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት እየተወሰደ ያለው ኦፕሬሽንም ጠላትን ከንጹሃን ዜጎች በመለየት እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር መንገሻ ፈንታው በበኩላቸው፤ የተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠያቂነትን የማስፈን፣ የክልሉን አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለመመለስ ያለመ ነው።

በዚህም ስምሪት የሚሰጡ የቡድኑ አመራሮች፣ ተከታይ ጀሌዎችና በመንግስት ተቋማት፣ በንግድ ድርጅቶችና ሌሎች የስራ ዘርፎች የተሰማሩ የቡድኑ የገንዘብና የመረጃ ምንጭ የሆኑ አካላት ላይ ያተኮረ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህም በክልሉና በህዝቡ ላይ ባለፉት 14 ወራት የደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመትን በመግታት ወደ ተሟላ ሰላምና ልማት በመሸጋገር የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ መሆኑን አስረድተዋል።

ፅንፈኛ ቡድኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የመንግስት ተቋማትን ከማውደምና ከመዝረፍ ባሻገር ህጻናት እንዳይማሩ በማድረግ የክልሉን ተወዳዳሪነት በዘላቂነት እየጎዳው መሆኑን ህዝቡ መረዳት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ለኦፕሬሸኑ መሳካት ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ያገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና መላው የክልሉ ህዝብ የመከላከያ ሰራዊቱንና የክልሉን የፀጥታ ሃይል መረጃ በመስጠትና በሌሎች ጉዳዮች እንዲተባበሩ ጠይቀዋል።

የተጀመረው ኦፕሬሽንም ክልሉ ወደ ዘላቂ ሰላምና ልማት ስራ እስኪመለስ ድረስ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ ተመልክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም