ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻባብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት ገለጸች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻባብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት ገለጸች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ግብጽ ወደ ቀጣናው የምትልካቸው የጦር መሳሪያዎች እንደ አልሻባብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ስጋት እንዳላት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት አንደኛ ፀሐፊ (ከፍተኛ ዲፕሎማት) ኩራባቸው ትርፌሳ ገለጹ።
በኒውዮርክ ሲካሄድ የቆየው 79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት ተጠናቋል።
ኢትዮጵያ በተመድ የግብጽ ተወካይ ላቀረቡት ሐሰተኛ ክስ በጠቅላላ ጉባኤው የስነስርዓት ደንብ ያላትን የመጀመሪያ ምላሽ መብት ተጠቅማ (First right of reply) በተመድ የኢትዮጵያ ምክትል ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ዮሴፍ ካሳዬ አማካኝነት ምላሽ መስጠቷ ይታወቃል።
ኢትዮጵያ የግብጽ ተወካይ በድጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ለሰጡት አስተያየት የሁለተኛ ምላሽ መብቷን ተጠቅማ (Second right of reply) መልስ ሰጥታለች።
ግብጽ በቀጣናው እና በአፍሪካ ቀንድ መሳሪያዎችን በመላክ እያደረገች ያለው እንቅስቃሴ አደገኛና ኢትዮጵያ መሳሪያዎቹ እንደ አልሻባብ ያሉ የሽብርተኛ ቡድኖች እጅ ሊገቡ እንደሚችሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ጽህፈት ቤት አንደኛ ፀሐፊ (ከፍተኛ ዲፕሎማት) ኩራባቸው ትርፌሳ ገልጸዋል።
የግብጽ በናይል ወንዝ ላይ የቅኝ ግዛት ዘመን ሕጎችን የሙጥኝ በማለት ብቻዬን ልጠቀም አካሄድ ተቀባይነት እንደሌለውም አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቶችን በፍትሐዊነት እና በእኩልነት በመጠቀም ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንደምታከብርም ተናግረዋል።
ስለሆነም ኢትዮጵያ የውሃ ሀብቷን ፍትሐዊነት እና እኩልነትን ባረጋገጠ መልኩ መጠቀሟን እንደምትቀጥል ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ ሶማሊያን ጨምሮ በቀጣናው ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ካላት ጽኑ ፍላጎት አንጻር የሰላም አስከባሪ ሰራዊት በመላክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑ ዓለም የሚያውቀው ሀቅ ነው።