በክልሉ አረጋዊያንን ለመደገፍ የገቢ ማስገኛ ማዕከል ማቋቋም እንዲሁም መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ባህር ዳር፤ መስከረም 21/2017 (አዜአ)፡- በአማራ ክልል አረጋዊያንን ለመደገፍ የገቢ ማስገኛ ማዕከል ማቋቋም እንዲሁም መብቶቻቸው እንዲከበርላቸው እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ገለጸ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ ወይዘሮ ንጹህ ሽፈራው በአገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የአረጋዊያን ቀን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም አረጋዊያን የካበተ ልምድና ትውልድን አሻጋሪ የሆነ እውቀት ባለቤቶች መሆናቸውን አውስተዋል።

በክልሉ አረጋዊያንን ለመደገፍ የገቢ ማስገኛ ማዕከል ከማቋቋም ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ አረጋዊያንን በማደራጀት መብቶቻቸውን ለማስከበር  እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ድጋፍ ለሚሹ አረጋዊያን ነጻ የጤና መድህን ሽፋንና የህግ አገልግሎት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አረጋዊያን በዕድሜ ዘመናቸው ለሀገራቸው በርካታ ውለታ የዋሉ በመሆናቸው ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋዊያንን መደገፍ የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆን የሁሉም ህብረተሰብና ተቋማት ሀላፊነት መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የበዓሉ መከበርም ህብረተሰቡ አረጋዊያንን የመደገፍ ሀላፊነቱን የበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል ግንዛቤ ለማስፋት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

አረጋዊያንን መንከባከብና መደገፍ ለአሁኑ ትውልድ እምቅ ልምዳቸውንና እውቀታቸውን እንዲያስተላልፉ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የበለጠ በተቀናጀ አግባብ ተጠናክሮ መቀጠል  እንዳለበት አሳስበዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ ጊዜ ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን "ፍቅርና ክብር ለአረጋዊያን" በሚል መሪ መሪ ሃሳብ እየተከበረ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም