በደብረ ብርሃን ከተማ የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቷል

ደብረ ብርሀን ፣መስከረም 21/2017(ኢዜአ) ፡- በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር የከተማ ግብርናን በማስፋፋት ለስራ እድል ፈጠራም አስተዋጽኦ እንዲኖረው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ገለፁ።

የከተማ አስተዳደሩ ግብርና መምሪያ በከተማ ግብርና ለሚሳተፉ ነዋሪዎች የግብርና መሳሪያዎች ድጋፍ አድርጓል፤ የግብርና እግዚብሽንም ተካሄዷል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ በድሉ ውብሸት እንደገለፁት፤ የከተማ ግብርና ምርታማነትን በማሳደግ ገበያን ከማረጋጋቱ ባለፈ ለሴቶች የስራ እድል በመፍጠር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ  እያገዘ ነው።

የከተማ ግብርና እና የበጋ መስኖ ልማትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በተቀናጀ አግባብ መረባረብ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ድጋፉ ዘርፉን ለማዘመን የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፤ ሙያዊ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ከራስ ባሻገር ለአካባቢ ገበያ የሚቀርብ ምርት ማምረት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የደብረ ብርሀን ከተማ አስተዳደር ግብርና መመሪያ ሃላፊ አቶ መርሻ አይሳነው በበኩላቸው፤ በውስን ቦታ የተጀመሩ  የከተማ ግብርና  እና የመስኖ ልማት ስራዎች የበለጠ ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በዛሬው ዕለትም 45 የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮችን ጨምሮ የአትክልት ዘር፣ የዶሮ ጫጩቶችና ሌሎች ድጋፎች መደረጋቸውን ገልፀዋል።

በአፄ ምሊኒክ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ መቅደስ ሽፈራው እንዳሉት፤ በከተማ ግብርና ዘርፍ ተሰማርተው በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናቸውን ከማረጋገጥ ባለፈ ትርፍ ምርት ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። 

''ሰላጣ፣ ቆስጣ፣ በቆሎ፣ ቦለቄ እና ሌሎችን በማልማት ወጪን መቀነስ ችያለሁ'' ያሉት ደግሞ የሰላም ጮራ ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ሀዋ መሐመድ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም