አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ):- የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሄኮ ኒትዝሺከን ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በአፍሪካ ቀንድ ወቅታዊ ሁኔታ እና በጋራ ፍላጎቶች ዙሪያ መክረዋል፤ ሚኒስትር ዴኤታው ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እየተጫወተች ያለውን ቁልፍ ሚና አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ከሌሎች አካላት ጋር ያላትን ትብብር የበለጠ በማሳደግ በአፍሪካ ቀንድ ልማት፣ ደኀንነት እና ብልጽግና እንዲረጋገጥ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ጀርመን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን እያደገ የመጣውን ስትራቴጂካዊ አጋርነትንም አድንቀዋል።
የጀርመን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሄኮ ኒትዝሺከ በበኩላቸው የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ የሚሆነው ቀጣናዊ አንድነት ሲጠናከር መሆኑን ገልጸው፤ ለቀጣናው ደኅንነት መረጋገጥ የኢትዮጵያ ሚና ወሳኝ መሆኑን በውይይቱ ላይ መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።