በሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮ በጋ ወራት ከ43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ይለማል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሸዋ ዞን በዘንድሮ በጋ ወራት ከ43 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ይለማል
ደብረ ብርሀን ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ):- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በተያዘው የበጋ ወራት 43 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በበጋ ወራት የመስኖ የግብርና ልማት ተግባራት ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በደብረ ብርሃን ከተማ ተካሄዷል።
የዞኑ ግብርና መመሪያ ሀላፊ አቶ ታደሰ ማሙሻ እንደገለፁት፤ የበጋ መስኖ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ በተሻለ ቅንጅትና ቴክኖሎጂ ታግዞ ስራው ይከናወናል።
ለዚህም ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን ለአርሶ አደሩ ሙያዊ እገዛ ከማድረግ ባሻገር ተገቢው ግብዓት በበቂ መጠን እንዲቀርብ እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በተያዘው የበጋ ወራት በበጋ መስኖ ከሚለማው መሬት ውስጥም 26 ሺህ ሄክታር በስንዴ ሰብል የሚለማ ሲሆን ቀሪው በሌሎች ሰብሎችና አትክልትና ፍራፍሬ እንደሚለማ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ከሚለማው መሬትም አንድ ነጥብ ስድስት ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ተናግረዋል።
የመስኖ ልማቱን ውጤታማ ለማድረግም ለአርሶ አደሩ አስፈላጊው ሁሉ ድጋፍ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ የኑሮው ደረጃ እንዲሻሻል ይሰራል ብለዋል።
በዚህም ለኢንዱስትሪ ግብዓት በስፋት የማቅረብ ምርት ከማምረት ባሻገረ ከተረጅነት ለመውጣትና የምግብ እህል ክምችት አቅምን ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
የባሶና ወራና ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ለገሰ ወልደማሪያም እንዳሉት፤ በበጋ ወራት የከርሰና የገፀ ምድር ውሃን በመጠቀም 1 ሺህ 74 ሄክታር መሬት በማልማት በምግብ ራስን ለመቻል እየተሰራ ነው።
የተጣለውን ግብ ለማሳካት 40 የውሃ መሳቢያ ጀነሬተሮች ለአርሶ አደሩ መቅረቡን ጠቅሰው፤ የመስኖ አውታሮችን የማጽዳትና የተፈጥሮ ማዳበሪያ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በ2016 የበጋ መስኖ ልማት በሄክታር የተገኘውን 40 ኩንታል ምርታማነት ወደ 45 ኩንታል ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የበጋ የመስኖ ልማትን ለማሳለጥ ከአርሶ አደሮች ጋር በስፋት መግባባት ላይ መደረሱን የገለፁት ደግሞ በዞኑ የአሳግርት ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ወሰኔ አምበርብር ናቸው።
በዞኑ ባለፈው ዓመት 36 ሺህ ሄክታር ማልማት እንደተቻለ የተጠቀሰ ሲሆን በዛሬው መድረክም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳታፊ ሆነዋል።