የድሬዳዋ ፖሊስ የትራፊክ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳልጥ ሶፍትዌር ወደ ተግባር አሸጋገረ

ድሬዳዋ ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ)፦ የድሬዳዋ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያበለፀገውን ዲጂታል የትራንስፖርት ስምሪት መቆጣጠሪያ ሶፍትዌር ወደ ስራ አሸጋግሯል።

ዛሬ ወደ ስራ የተሸጋገረው የትራንስፖርት ስምሪት መከታተያ እና ማስተዳደሪያ ስርዓት (ሶፍትዌር) በዋነኛነት የሌሊት ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችን እንቅስቃሴዎች እና የመረጃ ልውውጥ ፈጣንና ቀልጣፋ የሚያደርግ መሆኑ ተመላክቷል።

የበለፀገውን ሶፍትዌር መርቀው ስራ ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን እና ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ እንዲሁም የአስተዳደሩ የካቢኔ አባላት ናቸው።

አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ወደ ስራ የተሸጋገረው ቴክኖሎጂ ዘመናዊ የትራፊክ አስተዳደር ስርዓትን ለማስፈን ያስችላል።

የአስተዳደሩ ፖሊስ ድሬዳዋን ስማርት ሲቲ ለማድረግና ዲጂታል አገልግሎቶችን በየተቋማቱ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረውን የቴክኖሎጂ ጉዞ ዕውን በማድረግ ረገድ ቀዳሚ ተቋም መሆኑንም አንስተዋል።

የአስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ የድሬዳዋ ፖሊስ በዲጂታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ የአስተዳደሩና የአካባቢውን ሰላም እና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ እያከናወነ የሚገኘው ተግባር አበረታች ነው ብለዋል።

እነዚህን ስራዎች በማሳደግ እና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚያከናውናቸውን ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

አስተዳደሩም ለስራው መሳካት የሚያደርገውን የቅርብ ክትትልና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በማረጋገጥ።

የድሬዳዋን ሰላም በዘላቂነት ለመጠበቅ የተጀመሩ ጥረቶችን ለማስቀጠል ፖሊስ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የአስተዳደሩ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ ናቸው።

ወደ አገልግሎት የተሻገረው የቴክኖሎጂ ስርዓት የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች በፅሁፍ፣ በምስል እና በፎቶግራፍ ፈጣን መረጃዎች ከተቋሙ ጋር በመለዋወጥ አስተማማኝ  ሰላም በማስፈን ረገድ የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ያስችላል ብለዋል።

በተጨማሪም የትራፊክ ፍሰትን ቀልጣፋ እንዲሆንና አደጋን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ አበርክቶው የጎላ መሆኑን በማውሳት።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ሶፍትዌሮችን ለተቋሙ በማበልጸግ ተቋሙ ወደ ዲጂታል አገልግሎት እንዲሻገር እያበረከተ ለሚገኘው ማህበራዊ ኃላፊነትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ መምህርና የሶፍትዌር አበልፃጊ ቡድን መሪ አቶ ጌትነት ቶሎሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የድሬዳዋ ሁለንተናዊ ከፍታ እንዲረጋገጥና ዕድገቷ በአስተማማኝ ጎዳና እንዲጓዝ በጥናትና በምርምር የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በድሬዳዋ የሌሊት ታክሲ አሽከርካሪዎች "ሌሊቱ የእኛ ነው" በሚል መሪ ሃሳብ በመመራት ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እያበረከቱ የሚገኙት አስተዋጽኦ እንደ አገር በተሞክሮነት የተቀሰመና በሌሎችም የአገራችን ክልሎች ተግባራዊ እየሆነ የሚገኝ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም