የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል - ግብርና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ ይገኛል - ግብርና ሚኒስቴር
ድሬዳዋ ፤ መስከረም 21/ 2017(ኢዜአ)፦ በአገሪቱ በመተግበር ላይ የሚገኘው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እያገዘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።
የኢትዮጵያ የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ መርሃግብር (Ethiopian Food System Resilience Program) በኢትዮጵያ መንግስትና በዓለም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ በአብዛኛው የሀገሪቷ ክፍሎች በመተግበር ላይ ይገኛል።
በመርሃግብሩ አፈፃፀም እና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ የሚመክር የአምስት ቀናት አገር አቀፍ ጉባዔ በድሬዳዋ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ የተገኙት የግብርና ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከተማ በቀለ እንደተናገሩት፤ በመተግበር ላይ የሚገኘው የምግብ ስርዓት ማጠናከሪያ መርሃግብር በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናንና ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን እያገዘ ነው።
መርሃግብሩ በተለይም አገር በቀል የኢኮኖሚ ፓሊሲን ከግብ ለማድረስ ከተዘጋጀው የአስር አመት የግብርና ልማት ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ የሚካሄድ በመሆኑ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
መርሃግብሩ የምግብ ስርዓትን ስርነቀል በሆነ መንገድ ለመለወጥ፣ የስራ ዕድል ፈጠራን በብዛትና በጥራት ለማሳደግ እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያግዝ መሆኑን በመግለፅ።
በተለይ አገሪቷ በመተግበር ላይ የምትገኘውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ማህበረሰብ እና ኢኮኖሚ የመገንባት ሂደት በማገዝ ረገድ አበርክቶው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት በመርሃግብሩ የተሻለ አፈፃፀም የተመዘገበ ቢሆንም በቀጣይ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ የሚታዩ ውስንነቶችን በመለየት፤ የመፈፀም አቅም በማሳደግ፤ የግሉን ዘርፍ በማሳተፍና የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የሚፈለገውን ውጤት ለማስመዝገብ ተቀናጅቶ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በድሬዳዋ እየተካሄደ የሚገኘው የግምገማ መድረክም ለቀጣይ ስራዎች ምቹ ሁኔታዎች እንደሚፈጥር በመጠቆም ።
በውይይቱ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር በበኩላቸው መርሃግብሩ አነስተኛ የመስኖ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ፣ የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃን በማጠናከር፣ ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር ተጨባጭ ውጤቶች እያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በድሬዳዋ በመተግበር ላይ የሚገኘው መርሃግብሩ በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራትን እያሳኩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቶቹ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር አግዘዋል ብለዋል።
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎቹም የጎርፍ አደጋን እና የመሬት መንሸራተትን እየተከላከሉ መሆናቸውን በማንሳት።
በድሬዳዋ እየተካሄደ በሚገኘው ውይይት ላይ የግብርና ሚኒስቴር የመርሃግብሩ የአመራር አካላት፣ የዓለም ባንክ ተወካዮች፣ የክልሎች፣ የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ አስተዳደር የዘርፉ ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል።