በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የሚያቀርቧቸውን አጀንዳዎች ለመቀበል ዝግጁ ነን - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ 

አዲስ አበባ፤መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሚያቀርቧቸውን አጀንዳዎች ለመቀበል ዝግጁ ነን ሲሉ የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር  ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር አገራዊ ምክክሩን አስመልክቶ የተዘጋጀውን የሙዚቃ ክሊፕ (መዝሙር) ተረክቧል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ ኢትዮጵያውያን መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ የልዩነት ጉዳዮች ላይ መቀራረብ እንዲፈጠር ኮሚሽኑ እየሰራ ነው ብለዋል።  

ለዚህም የአሠራር ሥርዓት መመሪያዎችን በመዘርጋት ከአገር ውስጥ ባሻገር በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵውያንን ተሳትፎ ለማሳደግ ግንኙነት መሥርቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። 

በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካና በሌሎች ክፍላተ-ዓለማት ከሚኖሩ  ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጋር ከአሥር በላይ የበይነ-መረብ ምክክር መካሄዱን አስታውቀዋል። 

በርካታ የዓለም አገራት የውስጥ ችግሮቻቸውን በብሔራዊ ምክክር እልባት ሰጥተው የተሻለ ሰላም መገንባትና ዕድገት ማስመዝገብ መቻላቸውን አንስተዋል። 

በአሁኑ ወቅትም ኮሚሽኑ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች አጀንዳ የማሰባሰብ ምዕራፍ ማካሄዱን ጠቁመዋል። 

በአሁኑ ወቅትም በአፋር ክልል በሰመራ ከተማ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል። 

በዚህ ሂደትም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን የሚያቀርቡትን አጀንዳዎች ለመቀበል በራቸው ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል። 

በአዲስ አበባ ዳያስፖራዎች ማኅበር የተዘጋጀው የሙዚቃ ክሊፕ (መዝሙር) ለቀጣይ ሥራቸው በሚኖረው እገዛ መነሻነት ምስጋና አቅርበዋል። 

በአዲስ አበባ የዳያስፖራዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዝዳንት ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፤ ኮሚሽኑ ሲቋቋም የአገሬን ሰላምና ደኅንነት ያመጣል በሚል በታላቅ ደስታ የተቀበሉት መሆኑን አስታውሰዋል። 

ከሰላም ትርፍ እንጂ ኪሳራ የለም ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ኮሚሽኑ ለአገር ባለው ፋይዳ መነሻነት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች የሚችሉትን እገዛ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም