ለአረጋውያን አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ በመስጠት ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ለትውልዱ እንዲያስተላልፉ ማድረግ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ለአረጋውያን አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ በመስጠት ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ለትውልዱ እንዲያስተላልፉ ማድረግ ይገባል
ጋምቤላ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ) ፡- ለአረጋውያን አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ በመስጠት ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ለትውልዱ እንዲያስተላልፉ የማድረጉ ተግባር ሊጠናከር ይገባል ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።
''ክብርና ፍቅር ለአረጋውያን'' በሚል መሪ ሐሳብ ዓለም አቀፉ የአረጋውያን ቀን በብሔራዊ ደረጃ በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ዛሬ ተከብሯል።
ርዕሰ መስተዳድሯ በክብረ በዓሉ ላይ እንዳሉት አረጋውያን ያላቸውን የካበተ ልምድና ሀገርን የሚገነቡ እሴቶችን ለትውልዱ እንዲያስተላልፉ ምቹ ሁኔታዎችን ልንፈጥርላቸው ይገባል።
አረጋውያንን እንደማንኛውም የህብረተሰብ አካል በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች እኩል ተሳታፊ በማድረግ ያላቸውን ልምድና ዕውቀት ልንጠቀምበት ይገባልም ብለዋል።
አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ የትውልድ ቅብብሎሽ ቀጣይነት እንዲኖረው የማድረጉ ተግባር የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የክልሉ መንግስትም አረጋውያንን ለመደገፍና ለመንከባከብ ለሚደረጉ ጥረቶች ሁሉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ተወካይ እና በሚኒስትር ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ አቶ ጌታቸው በዳኔ በበኩላቸው አረጋውያን የረጅም ጊዜ እውቀትና የዳበረ ልምድ ባለፀጋ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ይህንን ልምድና ዕውቀታቸውን ለተተኪው ትውልድና ለማህበረሰቡ በማካፈል ለአገር ዕድገትና ልማት መፋጠን የድርሻቸውን እንዲወጡ ይሰራል ብለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያቤቱ የአረጋውያንን ህይወት ለማሻሻል የተለያዩ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ቀርዖ እየሰራ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማህበር ፕሬዘደንት አባ ሙዳ አበበ ሃይሉ እና ምክትላቸው አቶ ጌታቸው ክፍሉ በጋራ ባስተላለፉት መልዕክት አዲሱ ትውልድ ያለፈውን ትውልድ መንከባከብ አለበት ብለዋል።
በመሆኑም ተተኪው ትውልድ አረጋውያንን በመደገፍና በመንከባከብ በህይወት ዘመናቸው ያካበቱትን እውቀት ሊጠቀምበት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ምክር ቤት አባል ኮሎኔል አያሌው በላይ በበኩላቸው ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ በመጠበቅ ለትውልዱ ያስረከቡ አረጋውያን ውለታ ሊዘነጋ አይገባም ብለዋል።
በመሆኑም አዲሱ ትውልድ ቀደምት አባቶች ያቆዩዋትን ሀገር መጠበቅ ብቻ ሳይሆን ባለውለታ አባቶችን የመደገፍና የመንከባከብ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዓሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ በጋምቤላ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል።