በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማሳደግ የችግኝ እንክብካቤ ሥራ እየተሰራ ነው ---ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማሳደግ የችግኝ እንክብካቤ ሥራ እየተሰራ ነው ---ቢሮው
ባህር ዳር፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)--በአማራ ክልል በዘንድሮ የክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተተከሉ ችግኞችን የጽድቀት መጠን ለማሳደግ የአረምና የኩትኳቶ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ እስመለዓለም ምህረት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተለያዩ ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኞች ተተክለዋል።
በዚህም ህብረተሰቡን በማስተባበር 169ሺህ 361 ሄክታር መሬት በችግኝ መሸፈኑን ጠቅሰው፤ የተተከሉ ችግኞችን የፅድቀት ምጣኔን 85 በመቶ ለማድረስ የእንክብካቤ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ካለፈው ነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የአረምና የኩትኳቶ ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
እስካሁን በተደረገ ጥረትም በየአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮችን በማስተባበር ከ51 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የተተከለን የዋንዛ፣ ዝግባ፣ ወይራ፣ ኮሶ፣ ባህር ዛፍ፣ አካሽያ ዲከረንስና ሌሎች ችግኞችን የማረምና የመኮትኮት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
ለተተከሉ ሁሉም ችግኞች የመጀመሪያ ዙር የአረምና የኩትኳቶ ሥራ በተያዘው ወር ሙሉ በሙሉ ለማከናወን ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ገልፀዋል።
የእርጥበታማ ጊዜው ከማለፉ በፊት አርሶ አደሩ ቀሪውን ችግኝ የማረምና የመኮትኮት ተግባሩን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም አሳስበዋል።
በምዕራብ ጎጃም ዞን የሰከላ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አላምረው ፈንቴ በሰጡት አስተያየት፤ የተተከሉ ችግኞችን ተንከባክቦ ለማሳደግ የሁሉም ሀላፊነት ነው።
ቀደም ሲል የደንን ጥቅም በአግባቡ ባለማወቅ ደን ሲጨፈጨፍ መቆየቱን አስታውሰው፣ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ ልማት ባከናወኗቸው ስራዎች ችግኝን መትከልና ተንከባክቦ ማሳደግ ህይወትን ማስቀጠል መሆኑን መገንዘባቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም ዘንድሮ በክረምት ወቅት በግልና በወል መሬቶች የተከሏቸውን ችግኞች የመንከባከብ ሥራ እየሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን የፋርጣ ወረዳ አርሶ አደር እሱባለው ካሴ በበኩላቸው የደን መመንጠርን ከመከላከል ባለፈ ለችግኝ ተከላ በተሰጠው ትኩረት በአካባቢያቸው የተራቆቱ መሬቶች ቀድሞ ወደነበረው ልምላሜያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመቀናጀት በክረምት በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን የማረምና የመኮትኮት ሥራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በክልሉ በ2015 ዓ.ም የክረምት ወቅት በአረንጓዴ አሻራ ከተተከሉ ችግኞች 80 በመቶ ያህሉ ፀድቀው በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።