የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ - ኢዜአ አማርኛ
የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ስራ ተገብቷል - የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 21/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ የፀጥታና ደህንነት አካላት ቅድመ ዝግጅታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ መግባታቸውን አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው የፀጥታና ደህንነት አካላት የመስቀል ደመራ በዓል በሰላም መጠናቀቁን አስመልክተው በዛሬው እለት ባደረጉት ግምገማ ላይ ነው፡፡
የፀጥታና ደህንነት አካላት ባካሄዱት የተቀናጀ ኦፕሬሽን የመስቀል ደመራ በዓልን ለማደናቀፍ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሽብርና የፅንፈኛ ቡድን አባላትን እኩይ ዓላማ በአስተማማኝ ሁኔታ በማክሸፍ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች፣ ቦንቦች እና የፀጥታ አካላት የደንብ ልብሶች ጋር በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተገልጿል
ህብረተሰቡ ላደረገው ከፍተኛ ትብብርም የፀጥታና ደህንነት አካላት ምስጋና ማቅረባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
የመስቀል በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በድምቀት እንዲከበር የፀጥታና ደህንነት አካላት ከህብረተሰቡ ጋር በመተባበር የተቀናጀ ውጤታማ የፀጥታ ስራ መስራታቸውም ተገልጿል፡፡
መስከረም 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባና በቢሾፍቱ የሚከበረው የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ ኢሬቻ በዓላት ባህላዊ ስርዓታቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ሀይል አሰማርቶ ወደ ስራ መገባቱ ተመላክቷል፡፡
የኢሬቻ በዓል ከሚፈቅደው ባህላዊ ስርዓት ተቃራኒ የሆኑ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን ይዞ መገኘት ፈፅሞ የተከለከለ ሲሆን በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት የሌላቸው መሆኑን አስታውቋል፡፡
ይህንን በመተላለፍ በዓሉን ለማወክ በሚንቀሳቀስ ማንኛውም ግለሰብና ቡድን ላይ ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ተገልጿል፡፡
የፀጥታ አካላት በዓሉ በድምቀት እንዲጠናቀቅ በርካታ አጋዥ የህብረተሰብ ክፍሎች በፀጥታው ሥራ ላይ እየተሳተፉ እንደሆነ አንስተው ኅብረተሰቡ ከፖሊስ የሚተላለፉ የክልከላ መልዕክቶችን በማክበር ፀጥታን የሚያደፈርሱ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመጠቀም ጥቆማዎችን በፍጥነት በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች በአካል በማድረስ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀርቧል፡፡