ኢትዮጵያ እና ላኦስ በተለያዩ መስኮች በትብብር ለመስራት እንደሚፈልጉ ገለጹ

አዲስ አበባ ፤መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እና ላኦስ ግብርናና ኢንዱስትሪን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች በትብብር መስራት እንደሚፈልጉ አስታወቁ።

በጃፓን እና ላኦስ የኢትዮጵያ አምባሳደር ዳባ ደበሌ ከላኦስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፖክሳይ ካይካምፒቶን ጋር በሁለትዮሽ እና የጋራ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

አምባሳደር ዳባ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞችን እያካሄደች እንደምትገኝና በግብርና፣ ኢንዱስትሪና ንግድ ዘርፎች ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ላኦስ ያላቸውን የዲፕሎማሲ ትብብር ለማጠናከር መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

የላኦስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፖክሳይ ካይካምፒቶን ኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች የምትገኝና በአፍሪካ እምቅ ሃብት ያላት አገር መሆኗን ገልጸዋል።


 

ላኦስ ከኢትዮጵያ ጋር በግብርና ፣ ሃይድሮ ኤሌክትሪክ፣ ንግድና ቱሪዝም ዘርፎች የጋራ ጥቅሞችን መሰረት ባደረገ መልኩ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ ተናግረዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ለአምባሳደር ዳባ ደበሌ መልካም የስራ ጊዜ የተመኙ ሲሆን ለስራቸው ውጤታማነት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው መግለጻቸውን ቶኪዮ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

አምባሳደር ዳባ ለላኦስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፕሮቶኮል ሹም አምፓይ ኪንዳቮንግ ትናንት የሹመት ደብዳቤ ቅጂ ማስገባታቸው የሚታወስ ነው።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም