የሰላምና የአንድነት በዓል የሆነውን ኢሬቻ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምና የአንድነት በዓል የሆነውን ኢሬቻ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ የሰላምና የአንድነት በዓል የሆነውን ኢሬቻ ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አባገዳዎች ተናገሩ።
ኢሬቻ ከመስከረም ደማቅ መልኮች አንዱ ነው፤ የኦሮሞ ሕዝብ በአንድነት የሚያከብረው ልዩና የማንነቱ መገለጫ የሆነው የምስጋና፣ የሰላምና የወንድማማችነትም ምልክት ነው፡፡
በኦሮሞ ሕዝብ ባህል ዘንድ ኢሬቻ የሚከበረው ዝናብን፣ ሰላምን፣ ምርት እና የትውልድን ቀጣይነት የሚሰጥ ፈጣሪ በመሆኑ ጤናንና በረከትን የሚቸረው እሱ "ዋቃ" ወይም ፈጣሪ በመሆኑ ምስጋና ለማቅረብ ነው።
የገዳ ሥርዓት አንዱ አካል የሆነው ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ በረዥም ጊዜ የሕይወት ውጣ-ውረድ ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ሥርዓትና ልምድ ነው።
የመልካ (የውኃ ዳርቻ) ኢሬቻ በፀደይ ወቅት በሆራ ፊንፊኔና በሆራ አርሰዴ ይከበራል። በዚህም የክረምት ወራት የዝናብ፣ የደመና፣ የጭቃና የረግረግ ወቅት አልፎ ለፈካው ወራት በመብቃቱ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።
በዓሉን አስመልክቶ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኦሮሞ አባገዳዎች እንደሚሉት፤ ኢሬቻ የምስጋናና የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት ነው።
አባገዳ ለታ በየነ እንዳሉት፤ ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት ነፀብራቅ ከመሆኑም በላይ የኢትዮጵያውያንና የመላው ዓለም ቅርስ ነው።
በኢሬቻ የማክበሪያ ሥፍራ ሰላምና አንድነት ይሰበካል፤ ሕዝቡ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ለፈጣሪው ምስጋና ያቀርባል ነው ያሉት።
ሕዝቡ ወደ በዓሉ ማክበሪያ ሥፍራ ሲሄድ እርጥብ ሳር ይዞ፣ የሀገር ባህል ልብስ ለብሶ፣ የሰላም፣ የአብሮነትና የምስጋና ዝማሬ እየተዘመረ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል።
ይቅርታና የሰላም ዕለት በመሆኑ ይህንኑ የሕዝብ እሴት ለዓለም ማኅበረሰብ የምናሳይበት ነው ያሉት አባገዳው፤ ኢሬቻ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ፍላጎት የሚንፀባረቅበት አይደለም ብለዋል።
አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ ከመላው ሕዝብ ጋር ሆነው በዓሉን በጋራ ለማክበር ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
አባገዳ ሰቦቃ ለታ በበኩላቸው፤ በዓሉ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የሕዝቦችን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነት በሚያጠናክር መልኩ ማክበር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም አንድነት፣ አብሮነትን የበለጠ በማጉላትና ሕብርን በሚያሳይ መልኩ እንዲከበር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።
ለበዓሉ ታዳሚዎችና እንግዶች ተገቢውን አገልግሎት በመስጠት የምስጋናና የአብሮነት መገለጫ መሆኑን በተግባር ማሳየት እንደሚገባም ተናግረዋል።