ዲላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ተመራጭ ለማድረግ የመልሶ ማልማትና የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ዲላ ከተማን ለኢንቨስትመንትና ለኑሮ ተመራጭ ለማድረግ የመልሶ ማልማትና የኮሪደር ልማት ስራ እየተከናወነ ነው
ዲላ ፤መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦በጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማን ለኑሮ፣ ለስራና ኢንቨስትመንት ተመራጭ ለማድረግ የመልሶ ማልማትና የማስዋብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማው ህብረተሰብ ለኮሪደር ልማት ስራው ስኬታማነት ይዞታውን በማንሳት እና ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት ድጋፍ በማድረግ ተሳትፎውን እያጠናከረ መሆኑም ተመላክቷል።
የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ ምንተስኖት ከበደ ለኢዜአ እንዳሉት ከተማዋን ጽዱና ንጹህ እንዲሁም ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
"ከተማዋ ከተቆረቆረች ከ100 ዓመት በላይ ቢሆናትም የእድሜዋን ያህል መልመት አልቻለችም" ብለዋል።
ይህንን ታሪክ ለመቀየር በከተማው የሚገኙ ያረጁ አካባቢዎችን በማንሳት ለአልሚ ባለሀብቶች ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
ባለፉት ሶስት ወራትም በተደረገ ጥረት ከ13 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ የግለሰብና የቀበሌ ይዞታዎችን ከይገባኛል ነፃ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ከመልሶ ማልማት ሥራው በተጓዳኝ ለኮሪደርና አረንጓዴ ልማት 20 ኪሎ ሜትር የሚሆነውን ነጻ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤በዚህም ህብረተሰቡ ከ417 ቤቶችና ይዞታውን በማስጠጋት ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ድጋፍ ማድረጉንም አስረድተዋል።
በሀገር ደረጃ ከተሞችን ለኢንቨስትመንት ምቹ ለማድረግ እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ በዞኑም በመከናወን ላይ መሆኑን ያነሱት ደግሞ በጌዴኦ ዞን ከተማና መሠረት ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ረድኤት ክፍሌ ናቸው።
ከዚህ ቀደም በዲላ ከተማ ለኢንቨስትመንት ተብሎ ለባለሃብቶች የተሰጠው ይዞታ ወደ ልማት እንዲገባ መምሪያው ህጉንና አሰራሩን ተከትሎ ክትትል እያደረገ መሆኑንም አንስተዋል።
በከተማው ለተጀመሩ የልማት ስራዎች ስኬት ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም አቶ ረድኤት ጠይቀዋል።
የዲላ ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በከተማ አስተዳደሩ በተለምዶ 07 ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሰባት ሺህ ካሬ ሜትር የሚሆን መሬት ለአልሚ ባለሃብቶች ማዘጋጀቱንም ጠቁመዋል።
ከተማውን በመልሶ ማልማት፣በአረንጓዴና በኮሪደር ልማት ትግበራ ተመራጭና ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ያነሱት ደግሞ የከተማው ነዋሪ አቶ ደምሴ ሃንዲኖ ናቸው።
ልማቱ በሚካሄድበት ስፍራ የሚገኘውን የንግድ ተቋማቸውን አፍርሰው በማስጠጋት ለልማቱ የሚሆነውን ስፍራ ክፍት ማድረጋቸውንና በቀጣይም በከተማው በሚከናወኑ የልማት ተግባራት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ሌላዋ አስተያየት ሰጭ ወይዘሮ አስቴር ደመላሽ በበኩላቸው የመልሶ ማልማቱ ሥራ የከተማዋን ገጽታ ከመቀየሩ ባለፈ ውብና ጽዱ የሚያደርግ መሆኑን አንስተዋል።
ለልማቱ ይዞታቸውን በመልቀቅ በተሰጣቸው ምትክ ቤት ሕይወት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።