አርሰናል ከፒኤስጂ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከፒኤስጂ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አርሰናል ከፒኤስጂ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ዛሬ ይጀመራል።
አርሰናል እና ፒኤስጂ ከምሽቱ 4 ሰዓት በኤምሬትስ ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ በእግር ኳስ ቤተሰቡ በጉጉት የሚጠበቅ ጨዋታ ነው።
አርሰናል በመጀመሪያ የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታው ከአትላንታ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ ሲለያይ ፒኤስጂ ጂሮናን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ2016/17 የውድድር ዓመት በምድብ አንድ ተገናኝተው ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል ( አንድ አቻ እና ሁለት እኩል)።
የ44 ዓመቱ ስሎቬኒያዊ ስላቫኮ ቪንቺች ተጠባቂውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር ማምሻውን ሌሎች ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።
ስሎቫን ብራቲስላቫ ከማንችስተር ሲቲ፣ ባርሴሎና ከያንግ ቦይስ፣ ባየር ሌቨርኩሰን ከኤሲ ሚላን፣ ቦሩሲያ ዶርትሙንድ ከሴልቲክ፣ ኢንተር ሚላን ከሬድ ስታር ቤልግሬድ እና ፒኤስቪ አይንድሆቨን ከስፖርቲግ ሊዘበን በተመሳሳይ ከምሽቱ 4 ሰዓት ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ከብረስት እና ስቱትጋርት ከስፓርታ ፕራግ በተመሳሳይ ከምሽቱ 1 ሰዓት ከ45 ያካሂዳሉ።
የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዘንድሮው የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ድልድል ፎርማትን በማስቀረት 36 ክለቦች በ4 ቋቶች (Pots) በመከፋፈል እንዲጫወቱ የሚያደርግ አዲስ አሰራር ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።