ኮሚሽኑ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄድ ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ኮሚሽኑ በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄድ ጀመረ
ሠመራ ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ ከተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተለያዩ የህብረተሰብ ተወካዮች እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄድ ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር አይሮሪት መሐመድ (ዶ/ር) የምክክር ሂደቱ መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮችን መፍታት የሚያስችል አካታችና አሳታፊ ነው ብለዋል።
በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አበረታች የሚባሉ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱንም አስታውሰዋል።
በአፋር ክልል የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ለሚቀጥሉት ስድስት ቀናት የሚቆይ ሲሆን የተሳካ ምክክር የሚደረግበት እንደሚሆንም ተናግረዋል።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በክልሉ ከሚገኙ 49 ወረዳዎች የተወጣጡ ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑን ገልፀዋል።
ከዛሬ ጀምሮ በሚካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ተቋማትና ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችና የመንግስት አካላት የሚሳተፉበት መሆኑንም ኮሚሽነሯ ተናግረዋል።
መድረኩ ከአጀንዳ ማሰባሰብ ባለፈ ለሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎች ጭምር የሚመረጡበት መሆኑን አስታውቀው ተሳታፊዎቹ በቆይታቸው የዳበሩ ሐሳቦች እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።
ኮሚሽኑ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተመረኮዘ የምክክር መድረኮች እያካሄደ መሆኑንም ገልጸዋል።