በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 21/2017 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይካሄዳሉ።

ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽሬ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ውበቱ የሚመራው ፋሲል ከነማ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ቡድኑ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር ሁለት ግቦችን አስተናግዷል። ፋሲል በአራት ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በጌታቸው ዳዊት የሚሰለጥነው ስሑል ሽሬ በውድድር ዓመቱ እስከ አሁን ባደረጋቸው ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል።

በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።

ስሑል ሽሬ በአራት ነጥብ ተጋጣሚውን ፋሲል ከነማ ብዙ ጎል ባገባ በሚለው መለያ በልጦ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል።

ከምሽቱ 1 ሰዓት ባህር ዳር ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው የሚመራው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ አንድ ግብ ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አንድ ግብ ተቆጥሮበታል። ባህር ዳር በሶስት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በሁለተኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር አራፊ ቡድን የነበረው ሀዲያ ሆሳዕና በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው መቀሌ 70 እንደርታን 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወቃል።

በግርማ ታደሰ የሚሰለጥነው ሀዲያ ሆሳዕና በሶስት ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

በተያያዘም ትናንት በተደረጉ የሶስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች መቀሌ 70 እንደርታ ቅዱስ ጊዮርጊስን 1 ለ 0 ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ መድን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም