የአቪዬሽን እና የድንበር አገልግሎትና አስተዳደር ፕሮግራም የዘርፉን ደህንነት ይበልጥ የሚያስጠብቅ ነው - ዶክተር ዓለሙ ስሜ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ የአቪዬሽን እና የድንበር አገልግሎት አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም የዘርፉን ደህንነት ይበልጥ የሚያስጠብቅ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) ገለጹ።

በኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተዘጋጀውን ፕሮግራም የተመለከተ ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ እና ሚኒስትር ዴኤታዎች እንዲሁም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙ የአቪዬሽንና የድንበር አገልግሎትን በማዘመን ከንክኪ ነፃ ማድረግና ደህንነቱን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ተገልጿል።


 

የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችንና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን መነሻ በማድረግ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የገበያ ሁኔታ ትንተናዎችን፣ እየተስተዋሉ ያሉ ዋና ዋና የዘርፉ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ያካተተ መሆኑ ተመላክቷል።

የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በአቪዬሽን እና በድንበር አገልግሎት አሰራሮች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚቀርፍ በመሆኑ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብለዋል።

የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ፕሮግራሙን የዘርፉን አገልግሎት ለማሻሻልና ደህንነቱን ይበልጥ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ በበኩላቸው ፕሮግራሙ በአቪዬሽን እና በድንበር አገልግሎቶች ላይ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ተቀናጅተው እንዲሰሩ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፕሮግራሙ የተደራጀ ሀገራዊ መረጃ እንዲኖር በማድረግ፣ አገልግሎትን ለማዘመንና ደህንነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል መግለጻቸውን ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም