ቀጥታ፡

በክልሉ የተጀመረው የፍትህ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራር ጥራት ያለው የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ ነው

ባህር ዳር፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በፍትህ ተቋማት የተጀመረው ቅንጅታዊ አሰራር ለህብረተሰቡ ጥራት ያለው የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ መሆኑን የፍትህ ተቋማት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ገለጹ።

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትህ አካላት የትብብር ጥምረት መድረክ በሁለተኛ ቀን ውሎው በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ሲመክር ውሏል።

የአማራ ክልል ፍትህ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አያሌው አባተ እንደገለጹት፣ የፍትህ ተቋማት ቀደም ሲል በነበረው የአገልግሎት አሰጣጥ ቅንጅታዊ ክፍተት ይስተዋልባቸው ነበር።


 

ለዚህም ባለፉት ዓመታት የፍትህ ማሻሻያ ፕሮግራም ተቀርጾ ተግባራዊ ቢደረግም በሚፈለገው ልክ ባለመተግበሩ የሚፈለገውን ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ አስታውሰዋል።

ችግሩን ለማስተካከል ቅንጅታዊ አሰራርን የማጠናከር ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የፍትህ ተቋማት ክፍተቶቻቸውን አርመው ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጡ ያስችላል ብለዋል።

ከምርመራ እስከ ፍርድ ሂደት የሚስተዋለውን የፍትህ ጥራት ችግርን በዘላቂነት ለማቃለልም የተጀመረው ምክክርና ቅንጅታዊ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሙሏለም ቢያዝን በበኩላቸው እንዳሉት፤ የፍትህ ተቋማት ሥራቸውን በተጠናከረ ቅብብሎሽና በነፃነት እንዲሰሩ እየተደረገ ነው።


 

ይሁን እንጂ በወንጀል የተጠረጠሩ ግለሶቦችን በወቅቱ ለፍርድ አለማቅረብ፣ የፍርድ መዘግየትና የፍርድ ጥራት መጓደል ችግሮች እንደሚስተዋሉ ጠቁመው፤ ችግሮችን ለማረምና የተቀላጠፈ የፍትህ አገልግሎት ለመስጠት የጋራ መድረኩ መዘጋጀት አስፈላጊ ነው ብለዋል።

"የፍትህ አካላት ጥምረት ባለመጠናከሩ ያጎደልናቸው አገልግሎቶች አሉ" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስዬ ደጀን ናቸው።



 

በመድረኩ በዳኝነት፣ በፍትህ አካሉ፣ በፀጥታ መዋቅሩ፣ በፖሊስ የምርመራ ሂደት መታረም ያለባቸው ጉዳዮች በዝርዝር ቀርበው ውይይት እንደተደረገባቸው ገልጸዋል።

"በፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ሥራ ለመስራት እንደዚህ አይነት መድረኮች አስፈላጊ ናቸው" ሲሉም ገልጸዋል።

ሙያዊ ተልዕኮ ላይ ያተኮረ የፖሊስ መዋቅር እንዲኖር የሪፎርም ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚሽነር ደስዬ ጠቅሰው፣ የተጀመሩ መልካም ሥራዎችም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂክማ ከይረዲን በበኩላቸው፤ የሴቶችና ህፃናት ስትራቴጂን በአግባቡ መተግበር በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

በመሆኑም የወንጀል ህጉ በተቀመጠለት አግባብ በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን እንዲያቃልል የፍትህ አካላት ሚና ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል።

በዛሬው ውሎም የወንጀል መከላከል ህግ፣ በህገ ወጥ መንገድ የተገኘን ሃብት ማስመለስ፣ በሴቶችና ህፃናት ስትራቴጂ ፖሊሲና ሌሎች ሰነዶች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም