ኦምኒፖል ኩባንያ L410-NG የተሰኘችውን አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ሊያቀርብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኦምኒፖል ኩባንያ L410-NG የተሰኘችውን አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ሊያቀርብ ነው
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ ኦምኒፖል የተሰኘው የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያ ‘L410-NG’ የተሰኘች አነስተኛ ዘመናዊ አውሮፕላን ለኢትዮጵያ ገበያ ሊያቀርብ መሆኑን የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን አስታወቀ።
19 ሰዎችን የመጫን አቅም ያላት እና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ታስገኛለች የተባለችው ዘመናዊ አውሮፕላን ማስተዋወቂያ መርሐ ግብር ዛሬ ተካሂዷል፡፡
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ የንግድ ዘርፍ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ለማ ያደቻ፣ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ጌታቸው መንግስቴ፣ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክንና የግል አየር መንገድ ባለቤቶችና ስራ አስኪያጆች በትውውቁ ላይ ተገኝተዋል፡፡
አቶ ጌታቸው ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ ለረጅም ጊዜ የቆ ትብብር እንዳላቸው ገልጸው የዛሬው መርሃ ግብር በአቪዬሽን ዘርፉ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብለዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ለእይታ የመጣችው ይህችን አውሮፕላን በክፍተኛ አመራሮቹ ተጎብኝታለች።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕን ጨምሮ የግል አየር መንገዶች አውሮፕላኗን ለመግዛት ፍላጎት አሳይተዋል።
‘L410-NG’ ለመንገደኞች እና ለጭነት አገልግሎቶች መዋል የምትችል እንዲሁም ዘመናዊና ምቹ ስለመሆኗ መገለጹን ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።