የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 2 ለ 0 አሸነፈ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የጅቡቲ አቻውን 2 ለ 0 አሸነፈ
አዲስ አበባ ፤መስከረም 20/2017 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ አቻው ጋር ባደረገው የአቋም መለኪያ ጨዋታ 2 ለ 0 አሸንፏል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አጥቂው ናትናኤል ሰለሞን እና የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ደግፌ ዓለሙ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
በአሰልጣኝ ስዩም ከበደ የሚመራው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በ24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለመሳተፍ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።
ውድድሩ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በታንዛንያ ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።
ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።
በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።
በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት እንደሚሳተፉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።