የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት ጥሏል - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት ጥሏል - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ከለውጡ ወዲህ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ያካሄድነው የፀጥታና የደህንነት ተቋማት ሪፎርም ኢትዮጵያ ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር የሚያስችል መሰረት ጥሏል ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው የፀጥታ እና የደህንነት ተቋማት በአመራርና በሰው ኃይል የተጠናከሩ፣ አቅማቸው በቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ በደህንነት መሰረታዊና አንኳር ክህሎቶች የፈረጠሙ እና በዴሞክራሲያዊ መሰረት ላይ የታነፁ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ብቃት ያላቸው እንዲሆኑ ሰፊ ስራ ተስርቷል ሲሉ አስፍረዋል።
በውጤቱም ለሀገርና ለሕዝብ ጥቅም የቆሙ፣ ወገንተኝነታቸው ለህግ ብቻ የሆኑ፣ ጠላቶቻችን ኢትዮጵያ ላይ ፈፅሞ ክፉ እንዳያስቡ የሚያደርጉ፣ ለሀገር ጋሻ እና ጥላ የሆኑ ተቋማት ተገንብተዋል ሲሉም ገልጸዋል።
በቀጣይም ሕብረ-ብሔራዊ አንድነታችንን ይበልጥ ማጠናከር፣ ግጭት ቀስቃሽ አስተሳሰቦችንና ተግባራትን የሚጠየፍ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ባህል ማዳበር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በዘመናት መካከል በአባቶቻችን ደም እና አጥንት ታፍራ እና ተከብራ የመኖሯ እውነታ ከቶ እንዳይደፈር ማድረግ፣ ለዚህም ተቋማዊ አቅማችንንና የሕዝቡን ድጋፍ ይበልጥ እያጎለበቱ መሄድ ያስፈልጋል ብለዋል።