የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያው የአገር ልማትና እድገትን ማዕከል ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያው የአገር ልማትና እድገትን ማዕከል ያደረገ ነው

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያው ስፖርት ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና ያለውን ድርሻ በሚያሳድግ መልኩ መዘጋጀቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስትሯ ሸዊት ሻንካ ገለፁ።
አዲሱ የተሻሻለው የስፖርት ፖሊሲ በ2017 ዓ.ም ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቁሟል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በስፖርት ፖሊሲ እና አዋጅ ስመልክቶ ያዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ዛሬ ተካሄዷል።
በመድረኩ ላይ የስፖርት ማህበራት አመራሮች ተገኝተዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የስፖርት ፖሊሲ ማሻሻያው ስፖርትን ለአገራዊ ብልፅግና እና ልማት ያለውን ድርሻ ማሳደግን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።
የፖሊሲ ማሻሻያው በአደረጃጀት ለውጥ፣ ስፖርቱን እውቀት ባለው ሰው መምራት፣የማኅበረሰቡ የስፖርት እንቅስቃሴ ተሳትፎ እና የስፖርቱ ዘርፍ ከመንግሥት በጀትና ድጎማ ማላቀቅ ላይ ያሉ ችግሮችን መፍታትን መነሻ ማድረጉን አመልክተዋል።
በረቂቅ ስፖርት አዋጁም አገር አቀፍ የስፖርት ማህበራትና የስፖርት ተቋማት አስተዳደርና ቁመና፣ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አስተዳደር፣ የስፖርት ፋይናንስና የስፖርት ግጭቶች አፈታት መካተታቸውን ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎችየስፖርት ፖሊሲው አካታችነት ላይ የፓራ ኦሊምፒክና አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ግልፅ አሰራር መቀመጥ እንዳለበት ገልጸዋል።
የስፖርት መሠረተ-ልማት ዘመናዊነት የበለጠ የሚያሻሽሉ አሰራሮች በፖሊሲው መካተት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ የሚሳተፋ ፌዴሬሽኖችን የሚያበረታታና በገንዘብ የሚደግፍ አሰራርም በፖሊሲው መካተት እንዳለበት ነው ተሳታፊዎቹ ያነሱት።
የተሻሻለው የስፖርት ፖሊሲ በ2017 ዓ.ም ይፀድቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገልጿል።
በ1990 ዓ.ም የወጣው ሀገራዊው የስፖርት ፖሊሲ ስፖርቱ አሁን የደረሰበትን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ክለሳ እንደተደረገበት ተመላክቷል።
የስፖርት ፖሊሲው ዋንኛ ትኩረት ስፖርትን ማልማትና ስፖርትን ለልማት መጠቀም እንደሆነ ያስቀምጣል።