ቀጥታ፡

የኮሜሳ ሴቶች ቢዝነስ ፌዴሬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የሴቶች ቢዝነስ ፌደሬሽን ጉባኤ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።

የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ ከፌደሬሽን አባላት ጋር በጽህፈት ቤታቸው ተወያይተዋል።

በውይይቱ ላይ የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ቺካኩላ ሚቲ ተሳትፈዋል።

ውይይቱ እ.አ.አ ግንቦት ወር 2025 በኢትዮጵያ በሚካሄደው የኮሜሳ የሴቶች ቢዝነሽ ፈዴሬሽን ጉባኤ የተመለከተ መሆኑ ተገልጿል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ትስስርና የወጪ ንግድ ፕሮሞሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ የኢትዮጵያ መንግስት የኮሜሳ የሴቶች ቢዝነስ ፌደሬሽን ለሚያካሂደው ጉባዔ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

የፌዴሬሽኑ አባላት በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገነባውን የወጪ ንግድ ምርቶች ማሳያ ማዕከል መጎብኘታቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) እ.አ.አ በ1994 የተቋቋመ ሲሆን ግዙፍ የኢኮኖሚ እና ንግድ ማዕቀፍ በመፍጠር አገራት የሚገጥማቸውን መሰናክሎች መፍታት ዋንኛ ትኩረቱ አድርጎ ይሰራል።

በቀጣናዊ ትስስር የኢኮኖሚ ብልጽግናን ማምጣት ሌላኛው የድርጅቱ የትኩረት ማዕከል ነው።

ኮሜሳ ኢትዮጵያን ጨምሮ 21 አባል አገራት ያሉት ሲሆን አገራቱ ከ640 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ብዛት እና የአንድ ትሪሊዮን ዶላር አጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም