ቀጥታ፡

የቡና አምራቾችን በቅርበት በመደገፍ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ሽመልስ አብዲሣ 

አዲስ አበባ ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦የቡና አምራቾችን በቅርበት በመደገፍ የምርት ጥራትና ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡ 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የቡና ምርታማነትና ጥራት ማሻሻያ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል። 

በዚህ ጊዜ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፤ ባለሃብቱ ዕውቀትና ቴክኖሎጂን በመጠቀም የቡና ምርታማነት ጥራትን በማስጠብቅ ሚናውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።

መንግስት የአርሶ አደሩን የቡና ምርታማነት ለማሳደግ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገርም ከዘርፉ የሚገኘውን የገቢ አቅም ለማሳደግ አልሚ ባለሃብቶች ተሳትፏቸው አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የክልሉ መንግስትም በቡና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ አልሚ ባለሀብቶች የገንዘብ ብድር፣ ከሊዝ ነፃ የመሬት አቅርቦትና ተያያዥ ድጋፎችን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የቡና ምርታማነት ለማሻሻል ከሚደረገው ጥረት በተጓዳኝም የቡና ምርት በዘመናዊ የግብይትና ህጋዊ የአሰራር ሥርዓትን የተከተለ እንዲሆን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የቡና ምርት ግብይት በዘመናዊና ህጋዊ የአሰራር ሥርዓት እንዲፈጸም ለማድረግ የሚደረገው ጥረትም የምርት ብክነትና ብልሽትን ለማስተካከል አይነተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል። 


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ የምታቀርበው የቡና ምርት እየጨመረ ነው ብለዋል።

በዚህም 2 ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮች የንግድ ፈቃድ በማውጣት የቡና ምርታቸውን በቀጥታ ለውጭ ገበያ በመላክ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። 

መንግስት ተግባራዊ ያደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የቡና ንግድና ኢንቨስትመንትን በማሳደግ ኢትዮጵያ በዓለም የቡና ገበያ ያላትን ዕድል  ለማስፋት አይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በአገሪቱ በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከ298 ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1ነጥብ 43 ቢሊየን  የአሜሪካን ዶላር ገቢ  መገኘቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም