ቀጥታ፡

ባህላዊ ዕሴቶችን ማልማትና መንከባከብ በህዝቦች መካከል ትስስርንና ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት መሠረት የሚጥል ነው

ሚዛን አማን ፤መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ ባህላዊ ዕሴቶችን ማልማትና መንከባከብ ባህሉን ይበልጥ የሚያከብር ትውልድ በመፍጠር በህዝቦች መካከል ትስስርንና ዘላቂ ሰላምን ለማጽናት መሠረት የሚጥል መሆኑ ተገለጸ።

የሸካቾ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሬ ባሮ" በሸካ ዞን ጌጫ ከተማ በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘውዴ እንዳሉት ባህል የማንነት መገለጫ የሆነ ውብ እሴት ነው።

በተለያዩ ብሔረሰቦች ውስጥ ያሉ ባህላዊ ዕሴቶችን መጠበቅና መንከባከብ የሚደማመጥና የሚከባበር ትውልድን ለመፍጠር የሚያስችል መሠረት የሚያስቀምጥ ነው ብለዋል።

"ማሽቃሬ ባሮ" የሸካቾ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ አብሮነት፣ ልማትና ሰላም ላይ ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲሠራ የሚያስችሉ ተግባራት በባህሉ መሠረት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ የሚገኙ ባህሎችን ማልማትና ማስተዋወቅ ላይ የክልሉ መንግስት ትኩረት አድርጎ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

የሸካቾ ዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሬ ባሮ" የያዛቸው የሰላም፣ የልማትና አብሮነት ዕሴቶች ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ አዎንታዊ ሚና የሚያበረክት እንደሆነም አመልክተዋል።

በ"ማሽቃሬ ባሮ" ውስጥ ያሉ ሀገር በቀል እውቀቶችን ለማሳደግ የማጥናትና የመሰነድ ሥራ ይሠራል ያሉት አቶ አልማው፤ በዚህ ተግባር ውስጥ ምሁራን ድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።


 

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ በበኩላቸው ባህልን መጠበቅ የሕዝቦችን የእርስ በእርስ ትስስር ከማጠናከር ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

ባህል የትናንት ማንነትን አጉልቶ በማሳየት ለቀጣዩ ትውልድ መቻቻልን፣ የሥራ ባህልና ወንድማማችነትን በማስተማር በጎ ሥነ ምግባርን የሚያላብስ መሆኑን ተናግረዋል።

ቢሮው ሁሉም ብሔረሰቦች ባህሎቻቸውን አውጥተው መጠቀም በሚችሉበት ሁኔታ ላይ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።


 

የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ በበኩላቸው ሸካቾ ከረጅም ዘመን በፊት ያከብር የነበረውን ሥርዓቱን አሁን መንግስት የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ዛሬ ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።

"ማሽቃሬ ባሮ" የተደበቁ ባህሎችን ወደ አደባባይ የማውጣት እድል መፍጠሩን ጠቅሰው፤ የዞኑን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋ ከባህልና ቱሪዝም ጋር በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲኖረው ዞኑ እየሠራ ነው ብለዋል።

በ"ማሽቃሬ ባሮ" ሥነ ሥርዓት ላይ "ዩቦ" የተሰኘ ባህላዊ ጭፈራ፣ የፈረስ ጉግስ እንዲሁም "ቲሞ" እና "ሼሮ" የተሰኙ ባህላዊ የቀጣይ ዓመት የሥራ እና ሥነ ምግባር አዋጅ ቀርበው የብሔረሰቡ ባህላዊ ንጉሥ ባደረጉት ምረቃ አዲሱን ዓመት ተቀብለዋል።

በአንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ በተከበረው የሸካቾ ዘመን መለወጫ "ማሽቃሬ ባሮ" ላይ የዞኑና የአጎራባች ዞኖች የባህል አባቶችና የኅብረተሰብ ተወካዮች እንዲሁም የክልሉና የፌዴራል መንግስት የሥራ ሃላፊዎች እና እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም