የተ.መ.ድ የልማት መርኃ-ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፉን ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
የተ.መ.ድ የልማት መርኃ-ግብር ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፉን ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት መርኃ-ግብር (ዩ ኤን ዲ ፒ) ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እያከናወነች ላለው ተግባር ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።
በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ የሚመክር የባለድርሻ አካላት የባለሙያዎች ፎረም ዛሬ ተካሂዷል።
የፎረሙ ሰብሳቢ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን፤ ፎረሙ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ምጣኔ ኃብት ልማትን ለመገንባት የምታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ የሚያስችል ትብብር ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለምታዘጋጃቸው ፖሊሲና ስትራቴጂዎች በተለይም የቴክኒክ፣ የፋይናንስና ሌሎች የዘርፉን ዓለም አቀፍ ልምዶች በማምጣት በትብብር ለመሥራት ዕድል እንደሚፈጥርም ገልፀዋል።
ዓለም አቀፍ ተቋማት ትብብራቸውንና የፋይናንስ ድጋፋቸውን በዘላቂነት እንዲያጠናክሩ ዕድል ይፈጥራልም ነው ያሉት።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በብሔራዊ ደረጃ ለምትተገብረው ዕቅድ የሚያስፈልገውን ፋይናንስ ለመሸፈን የልማት አጋሮች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ዕቅዱን ለመተግበር ለአሥር ዓመት 316 ቢሊየን ዶላር የሚያስፈልግ ሲሆን፤ 253 ቢሊየን ዶላር ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የሚገኝ በመሆኑ ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የፎረሙ ጸሐፊ የተባበሩት መንግሥታት የልማት መርኃ-ግብር (ዩ ኤን ዲ ፒ) የኢትዮጵያ ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በአረንጓዴ አሻራና ሌሎች ዕቅዶች የምታከናውነው ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልፀዋል።
ዩ ኤን ዲ ፒ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን በመከላከል አረንጓዴ ልማትን ለመገንባት የያዘችውን ዕቅድ እውን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በማስተባበር ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የሚቋቋም አረንጓዴ ምጣኔ ኃብት ለመገንባት በሚከናወኑ የባለሙያዎች ፎረሙ፤ በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሰሩ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮችና የመንግሥት ተቋማት በአንድነት የሚሰሩበት ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2011 የተቋቋመ ሲሆን፤ በየሦስት ወሩ በመገናኘት በኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ትግበራ ላይ ውይይት በማድረግ የአፈጻጸም አቅም የሚያጠናክር ነው።