ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ከአሳሳች ግለሰቦች እንዲጠነቀቁ አሳሰበ - ኢዜአ አማርኛ
ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ከአሳሳች ግለሰቦች እንዲጠነቀቁ አሳሰበ
አዲስ አበባ፤መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ደንበኞቹ ከአሳሳች ግለሰቦች እንዲጠነቀቁ አሳስቧል።
ባንኩ በማህበራዊ ትስስር ገፁ እንዳለው፥ አንዳንድ አሳሳች ግለሰቦች የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም የገንዘብ እና የመረጃ ስርቆት ተግባር ይፈፅማሉ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን በመጠቀም እና አሳሳች ማስታወቂያዎችን በማሰራጨት የማታለል ሙከራዎች በስፋት እየታዩ ነው።
እነዚህ አታላይ ግለሰቦች በምስሉ እንደሚታየው "የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መጠይቅ በመሙላት የገንዘብ ስጦታ ታገኛላችሁ" የሚል አሳሳች መልዕክት እያስተላለፉ ነው።
እነዚህ ግለሰቦች የባንኩን ስም እና ዝና በመጠቀም የተለያየ ሕገወጥ ዓላማቸውን ለማስፈፀም ከሚያደርጉት ሙከራ ደንበኞች ራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ባንኩ አሳስቧል።
ደንበኞች መሰል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ትክክለኛነቱን ሳያረጋግጡ ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ በመቆጠብ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ በመሄድ አሊያም በ951 የባንኩ የደንበኞች ጥሪ ማዕከል በመደወል ስለሁኔታው ማጣራት እንዳለባቸውም ጠቁሟል።
በተጨማሪም ደንበኞች የባንኩን ትክክለኛ የማኅበራዊ ትስስር ገፆች ብቻ በመከተል ከእነዚህ አሳሳች ግለሰቦች ራሳቸውን መጠበቅ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመላክቷል።