የኢትዮጵያን የህዋ ሳይንስ ዘርፍ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ ነው

አዲስ አበባ፤መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያን የህዋ ሳይንስ ዘርፍ ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ ተግባራት በስፋት እየተከናወኑ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲቲዩት ከአፍሪካ ስፔስ ሊደርሺፕና ናይጄሪያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር "ዓለም አቀፍ የስፔስ ትብብርን ማሳደግ" ላይ ያተኮረ ስልጠና አስጀምሯል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩን አለማየሁ (ዶ/ር)፤ ህዋ (ስፔስ) የትኛውም አገር የኔ ብቻ ነው የማይሉት የሰራ ሁሉ ሊጠቀምበት የሚችል መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ላይ "የሰራ የሚያገኝበት ያልሰራ ደግሞ የማይጠቀምበት" በመሆኑ በትብብር በመስራት በጋራ መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅንጅት የሚሰሩ ስራዎች የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቅሰው፥ ከአፍሪካ ስፔስ ሊደርሺፕና ናይጄሪያ ኤምባሲ ጋር በመተባበር የተጀመረው ስልጠና ለዘርፉ ጠቀሜታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የህዋ ሳይንስ አሁን ያለበትን ደረጃ በዘርፉ ኢንቨስት ያደረጉ ተጽእኖ ፈጣሪ እንዲሆኑ ጠቅሰው፥ በኢትዮጵያም ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የዛሬው ስልጠናም በህዋ ሳይንስ፣ በህዋ ዲፕሎማሲና የህዋ አስተዳደር ላይ ያተኮረ አለም አቀፍ የግንዛቤ መድረክ መሆኑን ጠቁመው፥ ከዘርፉ የሚገኘውን ጠቀሜታ ለማሳደግ የሚከናወነውን ስራ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲቲዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልረዛቅ ኡመር፤ የኢትዮጵያ የዘርፉ እንቅስቃሴ በምሳሌነት የሚጠቀሱ መሆኑን ገልጸዋል።

በ21ኛው ክፍለ ዘመን ህዋ መልካም እድሎችና ተግዳሮቶችም እንዳሉት ጠቁመው በኮሙኒኬሽን፣ በግብርና፣ በህክምና እና በትምህርትና ሌሎችም ዘርፎች መልካም እድሎች ያሉት መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም ሰፊውን የህዋ አድማስ ለመጠቀም ዘርፉ ከሚጠይቀው የቴክኖሎጂና ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አንጻር አገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም