ቀጥታ፡

በአፋር ክልል ከነገ ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ ይካሄዳል - የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ሠመራ ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፡- በአፋር ክልል ከነገ መስከረም 21 ቀን 2017ዓ.ም ጀምሮ የአጀንዳ ማሰባሰብ መድረክ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አይሮሪት መሐመድ(ዶ/ር) በአፋር የአጀንዳ ማሰባሰቡን ሂደት አስመልክተው ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነሯ በመግለጫቸው በክልሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ባሉበት ከነገ መስከረም 21 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ  የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ይካሄዳል ብለዋል።

በመድረኩ ከ49 ወረዳዎች የተመረጡ ከ800 በላይ የህብረተሰብ ተወካዮች እንዲሁም ከ700 በላይ የሚሆኑ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት መሆኑንም አንስተዋል ።

በመግለጫቸው እንደጠቀሱት ይህ የምክክር መድረክ የህብረተሰብ ተወካዮች ለሀገራዊ መግባባት ይበጃሉ ያሏቸውን ሐሳቦችና መሠረታዊ ሐገራዊ ጉዳዮችን በአጀንዳነት አንስተው በህዝባዊ ውይይቱ የሚዳብርበት መሆኑን ገልፀዋል።

ለተከታታይ ስድስት ቀናት በሚቆየው በዚህ ሀገራዊ የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ ሀገራዊና ክልላዊ ፋይዳውን በመረዳት ከህብረተሰቡ የተወከሉት ተሳታፊዎች በንቃት መሳተፍ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን  አዲስ አበባን ጨምሮ  ከበርካታ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች  የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በማሰናዳት ከባለድርሻ አካላት የተሰበሰቡ አጀንዳዎችን መረከቡ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም