ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ያደርጋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከጅቡቲ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ዛሬ ያከናውናል።

የሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

24ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ከመስከረም 26 እስከ ጥቅምት 10 ቀን 2017 ዓ.ም በታንዛንያ ይካሄዳል።


 

ኢትዮጵያ በምድብ 2 ከዩጋንዳ፣ ብሩንዲና ደቡብ ሱዳን ጋር ተደልድላለች።

በምድብ 1 ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ በምድብ አንድ ተደልድለዋል።

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ ለማጣሪያ ውድድሩ ዝግጅት በመጀመሪያ ዙር ለ38 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረጉ ሲሆን ተጫዋቾቹ ከመስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ልምምድ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

አሰልጣኝ ሥዩም ከቀናት በፊት ተጫዋቾችን በመቀነስ በውድድሩ የሚጠቀሙባቸውን የመጨረሻ 20 ተጫዋቾችን ለይተዋል።

ብሔራዊ ቡድኑ ለውድድሩ ዝግጅት የሚረዳውን የአቋም መለኪያ ጨዋታ ከጅቡቲ አቻው ጋር ዛሬ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።

በሴካፋ ዞን ማጣሪያ ለፍጻሜ የሚደርሱ ሁለት ሀገራት ለአፍሪካ ዋንጫ ያልፋሉ።

በአፍሪካ ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ 12 ሀገራት ይሳተፋሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም