ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በሕግና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ በትብብር መስራት ትፈልጋለች - አቶ ተስፋዬ ዳባ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በሕግና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ በትብብር መስራት ትፈልጋለች - አቶ ተስፋዬ ዳባ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከአዘርባጃን ጋር በሕግና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ዘርፍ በትብብር መስራት እንደምትፈልግ የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ዳባ ገለጹ።
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋዬ ዳባ የተመራው ልዑክ በአዘርባጃን እየተካሄደ ባለው 29ኛው ዓለም አቀፍ የአቃቤ ሕጎች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፈ ይገኛል።
በአቶ ተስፋዬ ዳባ የተመራ ልዑክ ከአዘርባጃን ጠቅላይ አቃቤ ህግ ካሚራን አሊዬቭ ጋር ተወያይቷል።
በኢትዮጵያ እና በአዘርባጃን መካከል የሁለትዮሽ ትብብር እያደገ መምጣቱን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው ትብብሩ በሕግና የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ዘርፍም ማስፋት እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሁለቱ ሀገራት በፍትሕ ዘርፍ በትብብር መስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እንዲፈራረሙም ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ግብዣ አቅርበዋል።
የአዘርባጃን ዋና ጠቅላይ አቃቤ ህግ ካሚራን አሊዬቭ በበኩላቸው የሁለቱ ሀገራት ትብብር እየተጠናከረ መጥቷል ብለዋል።
አዘርባጃን በአቃቤ ሕግ ቢሮዎች ያደረገቻቸውን መጠነ ሰፊ የአሰራር ማሻሻያዎች አስመልክቶ ለልዑኩ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቃቤ ህጉ በሕዳር ወር 2017 ዓ.ም በሚካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደንዛዥ ዕፅ እና ወንጀል ፅህፈት ቤት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው እንዲሳተፉ ጋብዘዋል።
በአቶ ተስፋዬ ዳባ የተመራው የኢትዮጵያ ልዑክ በአዘርባጃን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዋና መስሪያ ቤት ያለውን ሙዚየምና በአዘርባጃን ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ የምርመራ ቢሮዎችን መጎብኘቱን ከፍትሕ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አቶ ተስፋዬ ከጉባዔው ጎን ለጎን ከአዘርባጃን የፍትሕ ሚኒስትር ፋሪድ አህማዶቭ ጋር መወያየታቸው ይታወቃል።