ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 20/2017(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቀሌ 70 እንደርታ ከቀኑ 10 ሰዓት በድሬዳዋ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው ቅዱስ ጊዮርጊስ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንዱን ሲያሸንፍ በአንዱ ተሸንፏል።

በጨዋታዎቹ ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ ሶስት ግቦች አስተናግዷል።

በዳንኤል ፀሐዬ የሚሰለጥነው መቀሌ 70 እንደርታ እስከ አሁን ባደረጋቸው ሁለት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸነፍ በአንዱ ነጥብ ተጋርቷል።

ቡድኑ በሁለት ጨዋታ አንድ ግብ ሲያስቆጥር ሁለት ጎሎች ተቆጥረውበታል።

ከምሽቱ 1 ሰዓት ኢትዮጵያ መድን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ የሚመራው ኢትዮጵያ መድን በመጀመሪያ የሊጉ ጨዋታው ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር ያለ ምንም ግብ አቻ መለያየቱ ይታወቃል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በሊጉ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ሲሸንፍ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር ሶስት ግቦችን አስተናግዷል።

በዘሪሁን ሸንገታ የሚሰለጥነው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዘገብ ይጫወታል።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገ ቀጥሎ ሲውል ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ፋሲል ከነማ ከስሑል ሽሬ ከቀኑ 10 ሰዓት እንዲሁም ባህር ዳር ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ከምሽቱ 1 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የሊጉ መሪ ድሬዳዋ ከተማ እና አዳማ ከተማ የሳምንቱ አራፊ ቡድኖች ናቸው።

የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ መስከረም 23 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆዩ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም