በትግራይ ክልል የደቡብ ምስራቅ ዞን ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል የደቡብ ምስራቅ ዞን ነዋሪዎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንዲፈቱላቸው ጠየቁ
መቀሌ፤ መስከረም 19/2017(ኢዜአ):- በትግራይ ክልል የደቡብ ምስራቅ ዞን ነዋሪዎች ያሉባቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲፈታላቸው ጠየቁ።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ከደቡብ ምስራቅ ዞን የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በክልሉ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ውይይት አድርገዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ በተለይም በአካባቢያቸው ህግን የሚጥሱ፣ የመሬት ወረራ የሚፈጽሙ፣ ሰላም እንዳይሰፍን የሚሰሩ አካላት እየተበራከቱ መጥተዋል ብለዋል።
ችግሮቹ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሠፉ በመሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የህዝቡ ፍላጎት ሰላም መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት ሰለሞን እምባዬ የእኛ የምን ጊዜም ፍላጎት ሰላም ነው ብሏል።
ወጣት አብርሃ ገብረ መድህን በበኩሉ፤ በአካባቢያቸው ያለው በወርቅ የበለጸገ መሬት በኢንቨስትመንት ስም እየተመዘበረ መሆኑን አመልክቶ፤ በተለይ የተጠያቂነት አሰራር በመጥፋቱ እንዲሁም የወጣቶች ህገ ወጥ ፍልሰት እየተበራከተ በመምጣቱ መፍትሄ ሊበጅለት እንደሚገባ ተናግሯል።
በአካባቢያቸው የመንገድ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ችግር፣ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለባቸውም ያወሱት ወይዘሮ ለምለም ተካ፤ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ችግሩን በሚገባ በማጤን መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፣ የተነሱትን ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ምዝበራና የጸጥታ ችግር በሚፈጥሩ አካላት ላይም ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
ዘመኑ የወጣቶች መሆኑን በሚገባ ተገንዝበን በተቀናጀ መልኩ ልናንቀሳቅሰው ይገባል፣ ተጠቃሚነቱንም ልናረጋግጥለት ይገባል ብለዋል።
አቶ ጌታቸው አክለውም ከሁሉም በላይ የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና ተስፋ የሚሠጡ ሥራዎች በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ከህዝባችን ጋር ተቀናጅተን እንሰራለን ያሉት አቶ ጌታቸው የልማት ሥራዎቻችንን አስፍተን እንቀጥላለን ብለዋል።
የተነሱ የፍትህ፣ የአስተዳደር፣ የጸጥታና የኢ-ፍትሃዊነት ችግሮችን ለማቃለል በትኩረት እንደሚሠራም ገልጸዋል።