ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሰረዘ - ኢዜአ አማርኛ
ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ተሰረዘ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 19/2017 (ኢዜአ)፦ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መሰረዙን የሊጉ አክሲዮን ማህበር አስታወቀ።
ውሳኔውን ተከትሎ መቻል እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፎርፌ ያገኙት ውጤት መሰረዙንም አመልክቷል።
ወልቂጤ ከተማ በሊጉ መወዳደር የሚያስችለውን አስገዳጅ የክለብ ላይሰንሲንግ ፈቃድ ባለማግኘቱ ምክንያት ሜዳ ገብቶ መጫወት አልቻለም።
በዚህም ምክንያት ወልቂጤ ከተማ በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ሳምንት መርሃ ግብር በመቻልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በፎርፌ ውጤት ተሸንፏል።
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ አንድ ክለብ ሁለት ጊዜ በተከታታይ ወይም በአንድ የውድድር ዓመት በተለያየ ጊዜ በጨዋታ ሜዳ ባለመገኘት ፎርፌ ከተሰጠበት ከውድድሩ መሰረዝና ወደ ከፍተኛ ሊግ የመውረድ ውሳኔ እንደሚተላለፍበት ይደነግጋል።
በመመሪያው መሰረት የውድድሩ የበላይ አወዳዳሪ አካል የሆነው የሊጉ አክሲዮን ማህበር ወልቂጤ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ መሰረዙን አስታውቋል። በውሳኔው መሰረት ክለቡ በውድድሩ ላይ አይሳተፍም።
ወልቂጤ ከተማ ከውድድሩ መሰረዙን ተከትሎ መቻልና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቡድኑ ያገኙት የፎርፌ ውጤት እንዲሰረዝ መደረጉን ገልጿል።
የ2017 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ18 ክለቦች እንደሚቀጥል አክሲዮን ማህበሩ አመልክቷል።